የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገልጿል፡፡
ዩኒቨርስቲው ከዓለም አቀፉ የኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ እውቅና ሰጭ ቦርድ /ABET/ በአራት የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን አስታውቋል።
ዩኒቨርሲቲው በባዮቴክኖሎጂ፣ በምግብ ሳይንስና ስነ ምግብ ፣ በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ እና በጂዮሎጂ በመጀመሪያ ድግሪ የትምህርት መርሃግብር ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር)፣ ይህ ከውጭ የሚመጡ ባለሙያዎችን በእኛ ሀገር የሚተካ፣ ባለሙያዎችንም ዓለም አቀፋ እውቅና ያላቸው እንዲሆኑ የሚያደርግ እውቅና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እውቅናውን ለማግኘት ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ በሂደት ላይ እንደነበር ገልፀው፣ ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮ መሆን የሚችል ስኬት መሆኑን ተናግረዋል ።
በባለፉት 5 አመታት ያከናወናቸውን ጠንካራ እና መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ከመዘኑ በኃላ የተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል ።
ለእውቅና የሚያበቁ መሰረታዊ መስፈርቶች ስምንት መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የፈተና እና የምዘና ስርዓት እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም እውቅናው ለኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
በምህንድስና ኮሌጅ ዘርፍ ያሉት የትምህርት ክፍሎችም ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑንም ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
በዳንኤል መላኩ