በግብር አሰባሰብ እና የጉምሩክ ስርዓትን ለማሻሻል የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡባቸው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ያዘጋጀው የመንግስት እና የግሉ የንግድ ዘርፍ ማህበራት የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው። መንግስት ከግሉ የንግድ ዘርፍ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችሉ አሰራሮችን እየተከተለ መሆኑ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እንዳስቻለ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ መሠረት ሞላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የተወከሉ አካላት በየተቋማቱ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችን የሚያሳዩ የመወያያ ሃሳቦች አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት እና የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት በጋራ “የግብር አሰባሰብ እና የጉምሩክ ስርዓት ለማሻሻል ፍትሃዊነት፣ ግልፅነት እና ቀልጣፋ አገልግሎት መዘርጋት በኢትዮጵያ” በሚል የተዘጋጀውን ጥናት አቅርበዋል።
በቀረበው የመወያያ ሀሳብ ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸው ሰፊ ለውጦች እንዲመዘገቡ እንዳስቻሉ ተናግረዋል።
በግብር አሰባሰብና በጉምሩክ አሰራር ስርዓት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች የተነሱ ሲሆን፤ ችግሮችን ለማሻሻል በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች ድርሻም ከፍተኛ እንደሆነም ተጠቁሟል።
በታምሩ ደምሴ