የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ከፍታ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ከፍታ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN ነሐሴ 27/2017

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ከፍታ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለፁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሀገርን በጥበብ በሚል የሚያዘጋጀው ወርሃዊ የስነ-ፅሁፍ መርሃ-ግብር “ህዳሴን በጥበብ” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

በመርሃ-ግብሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ አንጋፋው ደራሲና ተዋናይ ጌትነት እንየውን ጨምሮ የጥበብ ባለሙያዎች፣ ገጣሚያንና የኢዜአ የአመራር አባላትና ሰራተኞች ታድመዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በወቅቱ ህዳሴ ግድብ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለፍፃሜ መድረሱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራትና ደስታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከድህነትና ኃላቀርነት ማላቀቅና ወደ ስልጣኔ ማማ የማውጣት ጥረት በህዳሴ ግድቡ እውን ይሆናል ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት መልስ የሚሰጥና ወደ ከፍታዋ የሚመልስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑንም አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነትና አብሮነት ያረፈበት የጋራ አሻራ መሆኑንም ነው የገለፁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ በበኩላቸው ኢዜአ እንደ ሚዲያ ተቋም የግድቡን የግንባታ ሂደት ከመጀመሪያው ጀምሮ ቦታው ድረስ በመሄድ እየተከታተለ ለህዝብ መረጃ ሲያደርስ እንደነበር አስታውሰዋል።

ግድቡ አጋጥመውት የነበሩ ችግሮችን በጠንካራ አመራርና በህዝቦች የተባበረ ክንድ ማጠናቀቅ የትውልዱ ትልቅ ታሪክ ነው ብለዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍለው ለፍፃሜ ላደረሱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

በኪነ-ጥበብ መርሃ ግብሩ ላይ የህዳሴ ግድብን የተመለከቱ ግጥሞች፣ መጣጥፎች፣ ወጎችና አጫጭር ፅሁፎች በታዋቂ ገጣሚያንና ፀሐፍት ቀርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review