የዳንጎቴ ግሩፕ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን የመመስረት ልምድ

You are currently viewing የዳንጎቴ ግሩፕ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን የመመስረት ልምድ
  • Post category:ልማት

AMN-ነሐሴ 27/2017ዓ.ም

የዳንጎቴ ግሩኘ በአፍሪካ አንደኛ ፣ በአለም ከሚጠቀሱ ግዙፍ 5 የማዳበሪያ ፋብሪካዎች መካከል ደግሞ አንዱ መሆን የቻለውን ግዙፍ ፋብሪካ በናይጄሪያ አቋቁሟል።

በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ተመርቆ የተከፈተው ፋብሪካ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር ለመቋቋም አስተዋጽዖ እንደሚኖረው በወቅቱ ተዘግቧል። አፍሪካ ኒውስ በሰራው ዘገባ በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆነችው ሀገር ለዓለም አቀፉ አቅርቦት የበኩሏን አስተዋፅዖ የምታበረክትበትን የማዳበሪያ ፋብሪካ አስመረቀች ሲል አስነብቧል።

የካምፖኒው ባለቤት የሆኑት ቢሊየኔሩ አሊኮ ዳንጎቴ ፣  በምረቃው ወቅት አዲሱ ፋብሪካ ናይጄሪያን በማዳበሪያ ምርት ራሷን እንድትችል እና ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እና ለተቀረው አለም ለመላክ የሚያስችል አቅም ይኖረዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ፋብሪካው በሌጎስ ናይጄሪያ “በለኪ” ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ፣ በ500 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ መሆኑ ታውቋል።

ይህ የማዳባሪያ ፋብሪካ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባ ሲሆን የዳንጎቴ ማዳበሪያ ፋብሪካ በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ለማምረት በክፍል አንድ ተቋቁሟል።

ፋብሪካው ከገበሬ ማኅበራት፣ ከኮርፖሬት እርሻዎች፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ወይም የልማት አጋሮች ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪም በሁሉም የናይጄሪያ ክልሎች እንዲሁም በአፍሪካ የአፈር እና የእርሻ ምርትን ለማሻሻል ዘላቂነት ያለው አካሄድን ከሚፈልጉ አጋሮች ጋር እየሰራ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስትም የአፈር እና የእርሻ ምርትን በማሻሻል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማለም ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የግንባታ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈራርመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፋብሪካው የኢትዮጵያን ብልፅግና በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ ያስችላል ብለዋል።

ይህ ፋብሪካ በ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚገነባ በጀት ተይዞለታል። በዓመት ሦስት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ የማምረት አቅም አለዉ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የ40 በመቶ ድርሻ እና የዳንጎቴ ግሩፕ ደግሞ የ60 በመቶ ድርሻ እንዳለው ታውቋል።በኢትዮጵያ የሚገነባው ፋብሪካ የማምረት አቅሙ በዘርፉ ከፍተኛ አምራች ከሆነችው ናይጄሪያ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ተገልጿል ። ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ከሚያረጋግጡ አንኳር ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶች መካከል አንደኛው እና የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሚመልስ መሆኑም ታውቋል።

በሚቀጥሉት 40 ወራት ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ላይ የሚጨበጥ ለውጥ አምጥቶ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት የሚደግፍ መልካም ጅምር መሆኑን በስምምነቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review