የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የቻይና የነፃነት ቀንን አስመልክቶ በሚካሄደው ግዙፍ ወታደራዊ ሰልፍ ላይ ለመገኘት ቤጂንግ ገብተዋል።
ቀደም ሲል የደቡብ ኮሪያው የመረጃ ተቋም ተተኪያቸው ልትሆን እንደምትችል ከገለፃት ልጃቸው ጋር ነው ኪም ጆንግ ኡን ቻይና የገቡት። ኪም በዚህ መርሐ-ግብር ላይ መታደማቸው፣ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከሌሎች የዓለም መሪዎች ጋር የሚያገናኛቸው ይሆናል። ፕሬዝዳንት ሺ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መደምደሚያ ላይ ጃፓን በይፋ እጇን የሰጠችበትን 80ኛ ዓመት ለማክበር ሰልፉን ማዘጋጀታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ቻይና ይህን ወታደራዊ ሰልፍ የምታካሂደው፣ ፕሬዝዳንት ሺ የቤጂንግን ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳየት እያሰቡ ባሉበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑም ተመላክቷል። የዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ ዓለም አቀፉን የንግድ ሥርዓት እያደናቀፈ ነው በተባለበት በዚህ ወቅት፤ ሺ ቻይና አስተማማኝ የንግድ አጋር መሆኗን ለማሳየት ጥረት አድርገዋል።
ቤጂንግ የምታካሂደው ሰልፍ ቻይና በማንኛውም ግጭት አሜሪካን የመገዳደር አቅሟ እየጨመረ መምጣቱን ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑም ተጠቁሟል።
በታምራት ቢሻው