ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀመረ

You are currently viewing ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀመረ

AMN – ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።

በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ፣ የሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የአፍሪካና ሌሎች ሀገራት መሪዎች የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

ከዚህ ጉባኤ አስቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት ያዘጋጀው 2ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ ይገኛል። የአየር ንብረት ሳምንቱ “ውይይቶችን ወደ ተግባርና ውጤት መቀየር” በሚል መሪ ሀሳብ የአየር ንብረት ለውጥ ቃል ኪዳኖችን ወደ ሚጨበጥ የተግባር ውጤት መቀየር ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

የሀገራትን የልማት ትልሞችና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወደ ተጨበጠ ጠንካራ የለውጥ እርምጃ በማቅረብ ለ2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የፖሊሲ ሀሳቦች የሚዘጋጁበት ነው ተብሏል። በብራዚል ለሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-30) የጋራ አጀንዳን ለመቅረጽ እንደሚያግዝም ይጠበቃል።

በሳምንቱ የሀገራት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ምክክር፣ የጎንዮሽ ውይይት፣ የልምድ ልውውጦች፣ አውደ ርዕይና የትስስር ማጠናከሪያ መድረኮች የሚካሄዱ ይሆናል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመጀመሪያው የአየር ንብረት ሳምንት በፈረንጆቹ ግንቦት 2025 በፓናማ መካሄዱ እንደሚታወስ ተዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review