በአፍሪካ ህብረት እና በአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ ተገንብተው በቅርቡ አገልግሎት መስጠት በጀመሩት የገበያ ማዕከላትና የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች የንግድ ኤግዚብሽንና ባዛሮች ተከፍተዋል።
ኤግዚብሽንና ባዛሩን የከፈቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የገበያ ማዕከላቱ በዓላትን ጠብቀው ብቻ ሳይሆን ሁልግዜም ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ታስበው መገንባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሚያቀርቡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
በበዓላት ወቅት ገበያውን በማዛባት እና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በነዋሪው ላይ ጫና ለማድረግ የሚሞክሩ አንዳንድ አካላት እንደሚኖሩ ያነሱት ከንቲባ አዳነች፣ በምንም አይነት ሁኔታ ህዝቡ ላይ መሰል ጫና እንዳይፈጠር ይሰራልም ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ ለአንድ ሳምንት በሁሉም ክፍለ ከተሞች የንግድ ኤግዚብሽንና ባዛሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡
ኤግዚብሽንና ባዛሮቹ ሸማች እና አምራቹ በስፋት የሚገናኙበት እንዲሁም ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው እንደሚሆንም ገልጸዋል።
በሰብስቤ ባዩ