በበዓል ወቅት ሰዉ ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዳይኖር በትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ ሰውሰራሽ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየሰራ እንደሚገኝም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።
አምራቾች በቀጥታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ በማድረግ የተሻለ የግብይት ስርዓት መፍጠር መቻሉንም ገልፀዋል።
በዛሬዉ እለት የ2018 አዲስ ዓመት ንግድ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአፍሪካ ህብረት የገበያ ማዕከል በይፋ ተጀሞሯል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በቅርቡ ተመርቀዉ ስራ የጀመሩ የገበያ ማዕከላትም በአል ጠብቀዉ ብቻ ሳይሆን አመቱን ሙሉ በአዘቦት ቀን ጭምር አምራችና ሸማቹን በቋሚነት እንዲያገበያዩ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ሸማቾች ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሳይጋለጡ ወደነዚ ስፍራዎች ጐራ ብለዉ እንዲሸምቱ እና አምራቾች በቀጥታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡም ጥሪ አቅርበዋል።
የበአል ባዛሩ፣ በአፍሪካ ህብረት፣ በ4 ኪሎ ችሎት የገበያ ማዕከላት ጨምሮ በሁሉም ክፍለ ከተምች በሚገኙ የገበያ ማዕከላት መካሄድ ጀሞሯል።
በባዛሩ የተለያዩ የግብርና ፣የኢንዱስትሪ እንዲሁም ለበአል ወቅት የሚያስፈልጉ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማህበረሰብ መቅረቡንም ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በኤዚቢሽንና ባዛሩ መክፈቻ ላይ የተገኙት ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፣ በገበያ ማዕከላቱ ለበአል ብቻ ሳይሆን ሁሌም አምራችና ሸማቹ እንዲገበያይበት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ሸማቹ ህብረተሰብም በአቅራቢያዉ ወደ ሚገኙ ማዕከላት እየሄደ እንዲገበያይ ጥሪ አቅርበዋል።