ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ፋይናንስ ፍትሐዊነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለአቅም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ከአፍሪካ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

You are currently viewing ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ፋይናንስ ፍትሐዊነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለአቅም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ከአፍሪካ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

AMN – ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ፋይናንስ ፍትሐዊነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለአቅም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ከአፍሪካ ጎን እንዲቆም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ጥሪ አቀረቡ።

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ እንዳሉት፤ አፍሪካ ሁለተኛውን አህጉራዊ የአየር ንብረት ጉባኤ በመጪው ሳምንት ለማካሄድ ተዘጋጅታለች።

ከጉባኤው ቀደም ብሎ በተሰናዳው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት የሚደረጉ ውይይቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መሰረት የሚጥል ፍሬ ነገር እንደሚገኝባቸው ጠቁመዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች የምትገኘው አፍሪካ ድምጿ ጎላ ብሎ እንዲሰማና ምላሽ እንዲያገኝ በጋራ መነሳት እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጋራ ስንቆም የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ፍትሐዊ ምላሽ አጀንዳ እና ድምጽ በጉልህ ማሰማት እንችላለንም ብለዋል፡፡

አፍሪካ የአየር ንብረት ትግበራን፣ ፍትሐዊ ሽግግር እና የሀብት ማሰባሰብ ሥራን ትሻለች ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ለዚህ ፍትሐዊ ጥያቄ ዓለም ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

ለዚህ አጣዳፊ አጀንዳ ተገቢ እርምጃ ለመውሰድ ያለው ጊዜ አጭር መሆኑን በማንሳት፥ የአፍሪካ ህብረት ለስኬቱ ወሳኝ የአመራር ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ፋይናንስ ፍትሐዊነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለአቅም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ከአፍሪካ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ለመጪው ትውልድ ስንል የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየር መፍጠን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በተባበረ አቅም ጠንካራ፣ ዘላቂ እና የበለጸገች አፍሪካን እንዲሁም ለትውልዱ የምትመች ዓለምን መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review