የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 25 ሚሊዮን 343ሺ 216 ብር የዋጋ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ መያዙን አስታውቋል፡፡
ኮንትሮባንዱ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ3 ኢ.ት 60574 የፊት 38783 የኋላ ታርጋ ያሰረ ተሳቢ ተሽከርካሪ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ሲሞክር አዳማ ፈጣን መንገድ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የማዕከል ፈጥኖ ደራሽ ሬጅመንት አምስት ሻምበል ሦስት፣ ፀረ ኮንትሮባንድ እና የአዳማ ፈጣን መንገድ ተቆጣጣሪዎች በጋራ በመተባበር ባደረጉት ፍተሻ ልባሽ ጨርቆችን፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው እና ጥራታቸው ያልተጠበቁ መድሃኒቶችን መያዝ ችለዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ-3 ኢ.ት B79005 አይሱዚ ተሽከርካሪ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ 15 ሚሊዮን 394 ሺህ 500 ብር የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ ሞባይሎችን ሻግ አድርጎ ለማስገባት ሲሞክር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የኮንትሮባንድና ድንበር ቁጥጥር ፖሊስ መምሪያ የሬጅመንት 8 ሻምበል 3 ሻምበል ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ፍቃዱ ደሳለኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮንትሮባንድ በሀገር ኢኮኖሚና በዜጎች ጤና ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት በመገንዘብ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረቡን ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡