የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነት ለማጠናከር የዘርፉ ተዋንያን በኢ- ኮሜርስ ግብይት የጎላ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
”የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት ኤክስፖ 2017 ከነሐሴ 24 ጀምሮ በልዩ ልዩ መርሐ-ግብሮች በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የኤክስፖው አካል የሆነና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የፓናል ውይይት “ኢ- ኮሜርስና የዲጂታል አገልግሎቶች” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ መንግስት በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የንግድ ስርዓቷን በማዘመን ጥራት ያለው ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ እያሳደገች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር በንግድ ዘርፉ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ዓለም ከደረሰበት እድገት አንጻር ግን በኤሌክትሮኒክ የንግድ ግብይት ላይ ክፍተቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነት ለማጠናከር የዘርፉ ተዋንያን በኢ- ኮሜርስ ግብይት የጎላ ተሳትፎ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
መንግስት የኢ- ኮሜርስ የንግድ ስርዓትን ለማስፋፋት አስተማማኝ ተቋማዊ አደረጃጀት እየፈጠረ እንደሚገኝም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡