ህዝበ ሙስሊሙ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር እድገት በጋራ መስራት እንዳለበት ተገለጸ

You are currently viewing ህዝበ ሙስሊሙ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር እድገት በጋራ መስራት እንዳለበት ተገለጸ

AMN ነሐሴ 29/2017

1 ሺህ 500ኛው የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል /መውሊድ/ የእስልምና እምነት አባቶችና ተከታዮች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነስርዓቶች በታላቁ አንዋር መስጂድ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼኽ አብዱልከሪም ሼኽ በድረዲን በዚሁ ወቀት ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓሉ ሲከበር የነቢዩ መሐመድ አስተምህሮዎችን ተግባራዊ በማድረግ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ አቅመ ደካሞችን ማገዝ እንደሚገባ ገልጸዋል። የነቢዩ መሐመድ መወለድ ለዓለም ብርሃን መሆኑን በመጥቀስ፥ የዘንድሮው መውሊድ በኢትዮጵያ ልጆች የጋራ ትብብር የተሠራው ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ምርቃት ዋዜማ ላይ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያጠናቀቃቸው የልማት ስራዎች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸውም ኮርተናል፤ ተደስተናል ነው ያሉት። መውሊድ የአንድነት እና የመረዳዳት መገለጫ በዓል እንደሆነ በማንሳት፥ አብሮነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ሼኽ ፈትሁዲን ሀጂ ዘይኑ ሙቀና የዘንድሮ የመውሊድ በዓል ህዝበ ሙስሊሙ ታሪካዊ የመጅሊስ ምርጫ ባካሄደበት ወቅት መከበሩ ለየት ያደርገዋል ብለዋል። መንግስት የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረጉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን አመስግነዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በቀጣይም ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር እድገት በጋራ መስራት አለብን ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review