በአማራ ክልል የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የበደሉትን ሕዝብ በልማት መካስ እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ ነዉ

You are currently viewing በአማራ ክልል የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የበደሉትን ሕዝብ በልማት መካስ እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ ነዉ

AMN- ነሀሴ 29/2017 ዓ.ም

የቀድሞ ታጣቂዎች ከተሃድሶ ስልጠናው ባገኙት የጠራ ግንዛቤ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ገልጿል።

በጠዳ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከል ለአንድ ሳምንት የተሰጣቸውን ስልጠና ያጠናቀቁ የቀድሞ ታጣቂዎች የሽኝት ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ተወካይ አቶ ግዛቸው መኩሪያ እንደተናገሩት፣ የቀድሞ ታጣቂዎች ሰላም ፈላጊ መሆናችሁን በስልጠናው ሂደት ማረጋገጥ ተችሏል።

ከስልጠናው በኋላ ወደ ሕብረተሰቡ በመቀላቀል በምትጀምሩት አዲስ ህይወት የሠላም አምባሳደር በመሆን ሕብረተሰቡና መንግስትን በቅንነትና በታማኝነት ልታገለግሉ ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎች በአጭር ጊዜ ተቋቁመው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የጀመራቸውን የመልሶ ማቋቋም ስራዎች በትኩረት እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠናው አልፈው የበደሉትን ሕዝብ በልማት መካስ እንዲችሉ ኮሚሽኑ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሄዱበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ተገንዝበው የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች የሠላም ጥሪውን ከልብ ተቀብለው መግባታቸው አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን የገለጹት የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ በሪሁን መንግስቱ ናቸው።

የክልሉ መንግስት የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለው በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን አሰራር ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

የቀሩትም የሰላም ጥሪውን ተቀብለው እንዲገቡ በማድረግ በኩል የቀድሞ ታጣቂዎች የሠላም አምባሳደር በመሆን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ከሰልጣኝ የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል አገኘሁ መሠረት በሰጠው አስተያየት፣የተሀድሶ ስልጠናው በአስተሳሰብም ሆነ በአመለካከት የነበረንን ብዥታ በመቀየር ከተሳሳተ መንገድ ወጥተን የበደልነውን ሕዝብ መካስ እንድንችል ግንዛቤ አስጨብጦናል ብሏል።

በተሀድሶ ስልጠና ማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ላይ መከላከያን ጨምሮ የፌዴራል፣የክልል፣ የዞንና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review