ከቁጭት እንጉርጉሮ ወደ ተስፋ ዜማዎች

You are currently viewing ከቁጭት እንጉርጉሮ ወደ ተስፋ ዜማዎች

AMN – ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም

የአባይ ወንዝን በቁጭት እና በብሶት የሚያነሳሱ የኪነ ጥበብ ስራዎች ለዘመናት ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ መጀመሩን ተከትሎም ተስፋንና የወደፊት ብሩህ ጊዜን የሚያሳዩ የኪነ ጥበብ ውጤቶች ወደ ህዝብ ደርሰዋል፡፡

አንዳንዶቹ የኪነ ጥበብ ስራዎች ትንቢት ጭምር የሚመስሉ ነበሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የህዳሴዉን ግድብ ለመገደብ ኢትዮጵያውያን እንዲረባረቡ የሚቀሰቅሱ ናቸው፡፡

አባይ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ቁጭት ሆኖ ለዘመናት ኖሯል፡፡ ታዲያ የሀገሬዉ ህዝብ ቁጭቱን፤ ባስ ሲልም ቁጣውን በተለያዩ መንገዶች በአባይ ላይ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከያንያንም የህዝብ ነጸብራቅ ናቸው እና ቁጭታቸውን በኪነ ጥበብ ስራቸው ሲገልጹ ኖረዋል፡፡

አባይን ስደት ይብቃህ ለሀገርህ ስራ እያለች በማነጋገር ስትቆጭ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋዋን ስታነሳ የምትታየው ድምጻዊት ገነት ማስረሻ የህዳሴው ግድብ ከመጀመሩ ሶስት አመታትን አስቀድማ ትንቢት መሰል ዜማዋን ለህዝብ አደረሰች፤ ጭስ አልባው ነዳጅ እያለች፡፡

“ዓባይ ነጋ ጠባ ሀብቱን ያፈሰዋል

ጭስ አልባው ነዳጄ ብለው ምን ያንሰዋል”

እያለች ያዜመችዉ ድምጻዊት ገነት ማስረሻ የራሳችን ሃብት ሳንጠቀምበት ሃገሩን አቋርጦ ሲሄድ የኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭትን የሚያመላክት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ቁጭቱ ሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ራሱ አባይ ጋርም አለ እያለች የምታቀነቅነው ድምጻዊቷ በስተመጨረሻም ጥቅም መስጠት እንዳለበት፤

“ዘመን ቢያስታርቀን ከዓባይ ብንስማማ፣

ይዘን ተጠጋነው አካፋ እና ዶማ” እያለች በትንቢታዊ ዜማዋ ትገልጸዋለች፡፡

አባይ ለሀገሩ ሊሆን በጉባ በረሃ በኢትዮጵያውያን ላብ የህዳሴው ግድብ እውን ሊሆን ሲነሳ ታዲያ የኪነ ጥበብ ሰዎችም ቁጭታቸውን ወደ ተስፋ ለውጠው መጪውን ብሩህ ግዜ በማነሳሳት በግንባር ለግንባታ የተሰለፈውንም ደጀኑንም ህዝብ ሲያጀግኑ ቆይተዋል፡፡

በአባይ ጉያ ተወልዶ የአባይን ጉዞ እየተመለከተ ሲብሰለሰል ያደገው ድምጻዊ አሸብር በላይም፤

“አንተ የአገሬ ግርማ አንተ ያገሬ ኩራት

እንደተጣላ ሰዉ ስትሸሽ ለዘመናት

ሁሉም በጊዜዉ ነዉ ቅረብ እንተያይ

አባይ አባይ ማን አለ ለእኛ ከእኛ በላይ

እስኪ ተግበል አለን ጉዳይ” እያለ ለሃገሩ ተቆርቁሮ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት በዜማዉ ተቃኝቷል፡፡

አሸብር ሲገልጽ የቆየው ተስፋውን ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያውያን ግድቡን እውን ለማድረግ ክንዳቸውን አበርትተው በጋራ እንዲቆሙ ጭምር

“ክንድህን አሳየዉ የአገሬ ጀግና

አባይ ከወንዙ ላይ ቀጠሮ አለና” እያለ ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ ታሪክ መስራት ልማዳቸዉ መሆኑን በዜማው ጠይቋል፡፡

ዛሬ አባይ ግንድ ይዞ መዞሩን የኢትዮጵያን ገላ አጥቦ ጥቁር አፈሯን ለባዕድ መስጠቱን አቁሞ ተግ ብሎ ሀገሩን ሊያለማ በህዳሴው ግድብ እውን ሆኗል፡፡

ቁጭትና ተስፋቸውን በዜማቸው ሲያንጎራጉሩ ዛሬ የደረሱት ድምጻውያን ታዲያ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በኢትዮጵዊያን ተሳትፎ ተገንብቶ፣ እድሜ ሰጥቷቸዉ ከፍጻሜዉ የደረሰዉን ታላቁ የህዳሴ ግድ ከማየት በላይ ምን ደስታ አለ ብለዋል፡፡

በሸዋዬ ከፍያለዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review