የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን የሚሆነው ኢኮኖሚውን በወታደራዊ አቅም ማስደገፍ ሲቻል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኤሮ አባይ የድሮን ማምረቻን ጐብኝተዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እመርታ ከሚያሳዩ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ሀገሮች አንዷ መሆኗን ገልፀው፤ የጀመረችውን የእድገትና የብልፅግና ጉዞ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ የሚቻለው ኢኮኖሚውን በወታደራዊ አቅም እያስደገፉ መሄድ ሲቻል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለመበልፀግ የሚያስችል አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልፀው፤ በግብርና፣ በኢንዱስትሪው፣ በቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝምና በማዕድን እየታየ ያለው ውጤት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢኮኖሚንና ወታደራዊ አቅምን በማሳደግ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ሲደረስ ለባህል፣ ለኪነጥበብ፣ ለሙዚቃና መሰል መገለጫዎቻችን ትኩረት በመስጠት እያዳበሩ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖች በከፍተኛ ቁጥር እየተመረቱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ድሮኖቹ ከኦኘሬሽን ሥራ በተጨማሪ ለአካባቢ ቅኝት እና ለገቢያ የሚውሉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአንድ ጊዜ እስከ ሦስት ሺህ ድሮኖች አንዳንድ ኘሮግራሞችን ለማድመቅም እንደሚያገለግሉ ገልፀዋል፡፡
ድሮኖቹ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ውጪ ከውጪ የሚገዙ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ አሁን ላይ በራስ አቅም በሀገር ውስጥ በውስን ቦታ ሳይገደቡ ለቅኝት፣ ለኦኘሬሽን እና ለገበያ የሚውሉ በርካታ ድሮኖች እየተመረቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ድሮኖቹ የኢትዮጵያን ህልውናና ሉዓአላዊነት የሚገዳደር አደጋ ቢመጣ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የጀመርነውን ብልጽግና ለማስቀጠል የምንጠቀምበት መሣሪያ ይሆናልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ተስፋ ሰጪ ጅምር እያሳየች ስትሆን ጅምሩ እያደገና እየሰፋ የሚሄድና ከአለም ጋር ለመወዳደር የሚያስችለንን አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው
#Drone
#Military
#Defenceforce
#Ethiopia