አዲስ አበባን ለመኖር ምቹና አካታች ልማት ያላት ከተማ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing አዲስ አበባን ለመኖር ምቹና አካታች ልማት ያላት ከተማ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN-ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመስቀል አደባባይ – መገናኛ – ሳውዝ ጌት የተከናወነውን የኮሪደር ልማት በዛሬው ዕለት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡ ይህ የኮሪደር ልማት ብቻ ለ 23 ሺህ 622 ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱን ምረቃ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ የመዲናዋን ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለ እረፍት በትጋትና በጽናት እየተሰራ ነው፡፡ በዛሬው ዕለት የተመረቀው ከመስቀል አደባባይ – መገናኛ – ሳውዝ ጌት ኮሪደር በሁለተኛው ዙር ከተጀመሩ ስምንት ኮሪደሮች አምስተኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የተሰሩ የባቡር መስመር እና ሕንጻዎቹ ወደ መንገድ ተጠግተው መሰራታቸው የኮሪደር ልማት ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኮሪደር ልማቱን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቁመው ቦታው የእግር ኳስ ሜዳ፣ የመዝናኛ ካፍቴሪያ፣ የልጆች መጫወቻ ቦታ እና ሌሎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

ከ51 እስከ 60 ሜትር ስፋት ያለው 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን የዋና መንገድ፣ 16 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት የእግረኛ መንገድ፣ የድጋፍ ግምብ እና የመንገድ ዳር ስማርት ፖሎች እንደተገነቡለትም ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር፣ የባቡር ሀዲድ ላይ የተሽከርካሪና የእግረኛ ማቋረጫ፣ አመቺ የእግረኛና የሳይክል መጋለቢያ መንገዶችን ይዟል ማለታቸውን ከጽ/ቤታቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡:

#Development

#Corridor

#Addis Ababa

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review