የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በብራዚል የተለያዩ ከተሞች የባህል ትዕይንት ሊያቀርብ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በብራዚል የተለያዩ ከተሞች የባህል ትዕይንት ሊያቀርብ ነው

AMN ነሐሴ 30/2017

የኢትዮጵያ የባህል ልዑካን ቡድን በብራዚል የተለያዩ ከተሞች ከመስከረም 19 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም የባህል ትዕይንት ያቀርባል።

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ከብራዚል የባህል ሚኒስትር ማርጋሬት ሜኔዝስ ጋር በብራዚሊያ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት የባህል እና የሕዝብ ለሕዝብ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው። አምባሳደር ልዑልሰገድ ኢትዮጵያ እና ብራዚል ለ75 ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው በባህል ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የባህል ልዑካን ቡድን በብራዚል የተለያዩ ከተሞች ከመስከረም 19 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም የባህል ትዕይንት እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል። የባህል ልዑኩ የሚኖረው ቆይታ የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማሳደግ ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገልጸዋል። የብራዚል የባህል ሚኒስትር ማርጋሬት ሜኔዝስ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት በባህል እና በታሪክ የተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የነጻነት ተምሳሌት እና የአይበገሬነት ምልክት መሆኗን ጠቅሰው ይህም በብራዚል ታሪክ ላይ በጎ ተጽእኖ ማሳረፉን ጠቅሰዋል። የአገራቱን የባህል ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፣ የባህል ልዑካን ቡድኑ በብራዚል ለሚያደርገው የባህል ትዕይንት መንግስታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን በብራዚል የኢትዮጵያ ከኤምቤሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

#Ethiopia

#Culture

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review