በደቡብ አሜሪካ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አርጀንቲና በሜዳዋ ቬንዙኤላን 3ለ0 አሸነፈች። ሊዮኔል ሜሲ በሀገሩ ምድር ያደረገው የመጨረሻ ጨዋታ በተባለለት በዚህ ግጥሚያ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።
ቀሪውን አንድ ግብ ላውታሮ ማርቲኔዝ በስሙ አስመዝግቧል። ሊዮኔል ሜሲ ከዚህ በኋላ በሀገሩ ምድር ጨዋታ የሚያደርግበት እድል ያለ አይመስልም። በቦነስ አይረስ የሚገኘው ስታዲዮ ሙኑመንታል የታደሙ ደጋፊዎችም ይህን የተረዱ ይመስል የተለየ አቀባበል እና ድጋፍ አድርገውለታል።
ሜሲም ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ከልጆቹ ጋር ወደ ሜዳ በመግባት ልዩ ድባቡን አጣጥሟል። የ38 ዓመቱ ሊዮ ሜሲ በአጠቃላይ ለሀገሩ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛት 114 ያደረሰ ሲሆን የወደፊት ቆይታውን በቅርቡ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል። በሌሎች ጨዋታዎች ብራዚል ቺሊን አስተናግዳ 3ለ0 አሸንፋለች።

በካርሎ አንቸሎቲ ለምትመራው ብራዚል ኤስቴቫኦ ፣ ሉካስ ፓኬኤታ እና ቡርኖ ጉማኤሬሽ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ኡራጓይ ፔሩን 3ለ0 ፣ በተመሳሳይ ኮሎምቢያ ቦሊቪያን 3ለ0 ሲያሸንፉ ፓራጓይ እና ኢኳዶር 0ለ0 ተለያይተዋል። ለሊት የተደረጉ ጨዋታዎችን ተከትሎ ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ያለፉ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ስድስት ደርሰዋል።
በሸዋንግዛው ግርማ