ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር የምታደርገው ጨዋታ በተለያየ ምክንያት በሀገራችን ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። ግብፅ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ገንብታ ለትልልቅ ዋንጫዎች እና ውድድሮች እየተፎካከረች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንፃሩ ወጥነት የሌለው አቋም እያሳየ ይገኛል። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ቢገናኙም የሁለቱም ሀገራት ደጋፊዎች ጨዋታውን በተለየ ትኩረት ይጠብቁታል።
ለ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ አንድ ላይ የተደለደሉት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ዛሬ ሰባተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ግብፅ ካከናወነቻቸው ስድስት ጨዋታ 16 ነጥብ በመሰብሰብ ምድቡን ስትመራ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ የጨዋታ ብዛት ስድስት ነጥብ በማግኘት አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የሀገራቱ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በግብፅ 2ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ሁለቱ የካፍ መስራች ሀገራት በአጠቃላይ 19 ጊዜ ተገናኝተው 13ቱን ማሸነፍ የቻለችው ግብፅ ናት። ኢትዮጵያ ሦስት ጊዜ ማሸነፍ ችላለች። ዋልያዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ ግብፅን የረቱት ከሦስት ዓመት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ነበር።
ዛሬ ለ20ኛ ጊዜ የሚገናኙት ሁለቱ ሀገራት ጨዋታቸውን በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ያከናውናሉ። ጨዋታውን ደቡብ አፍሪካዊው ዋና ዳኛ ኦቦንጊል ቶም ይመሩታል።
በሸዋንግዛው ግርማ
#Sport
#Football