ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰላምን ማጽናት የጸጥታ ተቋማት ዋነኛ ተልዕኳቸው መሆኑን ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት የኢፌዴሪ የጸጥታ ተቋማት ዋነኛው ተልዕኮ ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ማጽናት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሄን በተመለከተ ከጸጥታ ተቋማት አመራሮች ጋር ሲደረግ የነበረው ውይይት ዛሬ መጠቃለሉን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ሰላምና ጸጥታ አስቻይ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ግብዐትም ነው፡፡ ይሄን ለማስከበር ሕዝባችን በባህሉና በዕሴቱ ላይ ተመሥርቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ፣ የጸጥታ ተቋማት ሚና የማይተካ ነው፡፡ የአሻጥር፣ የከተማና የገጠር ውንብድና፣ የኮንትሮባንድ፣ የሙስና፣ ሕገ ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር እና የመሳሰሉ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር የሕዝቡን ሰላም ማስከበር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ በስፋት ተነሥቷል፡፡

የሰዎችና የሸቀጦች ዝውውር ለብልጽግናችን ወሳኝ ናቸው፡፡ ስለዚህም በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ዝርፊያዎችን፣ እገታዎችን እና መሰናክሎችን በተጠና መንገድ መቆጣጠር ይገባናል፡፡ የጸጥታ ኃይላችን ሕዝቡን በየደረጃው በማስተባበር እነዚህን አካላት ከእኩይ ተግባራቸው መግታት፣ ብሎም ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቶበታል፡፡
ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን፣ የማዕድን ቦታዎችን፣ ኢንዱስትሪዎችን፣ የመኖሪያ አካባቢዎችን እና የሕዝብ መገልገያዎችን ደኅንነት ለመጠበቅና አገልግሎታቸው ያለ እንከን እንዲፈጽሙ ለማስቻል የጸጥታ አካላትና የየአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ወሳኝ መሆኑን በውይይቱ ወቅት ተነሥቷል፡፡
ሕዝቡ ሰላሙን በራሱ እጅ የማስከበር ፍላጎቱ፣ ዝግጁነቱና ዐቅሙ በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ተገምግሟል፡፡ ባህላዊና መንፈሳዊ ዕሴቶቹን በመጠቀም የታጠቁ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ እያደረገ ነው፡፡ ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ የአካባቢውን ሰላም እያስከበረ ነው፡፡ የጸጥታ አካላት ለሚያከናውኑት ሥምሪትም የመረጃና የሎጂስቲክስ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡ ይሄን የሕዝቡን ዐቅም ይበልጥ በሥልጠና በማጎልበት ለዘላቂ ሰላም መጠቀም እንደሚገባ በውይይቱ ማጠቃለያ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ በማሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሽብር ተግባር የሚፈጽሙትን ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት የተነሣ ሲሆን፣ በሳይበር ቴክኖሎጂ በኩል መከናወን የሚገባቸው የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራዎች ይበልጥ መጠናከር እንደሚገባቸው በውይይቱ ተመልክቷል፡፡ በአንድ በኩል የቴክኖሎጂ የመከላከያና መቆጣጠሪያ ሥራዎችን ለመሥራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሽብር ፈጣሪዎቹን ለሕግ ለማቅረብ የጸጥታ አካላት በጽኑ መሥራት እንዳለባቸው መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
የጸጥታ ተቋማት ወትሮ ዝግጁነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር በሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን በውይይቱ ተገምግሟል፡፡ ኢትዮጵያ ከዘመን ጋር የዘመኑ እና በሕገ መንግሥታዊ ዕሴቶች ላይ የተገነቡ የጸጥታ ተቋማት እየገነባች መሆኗ ተረጋግጧል፡፡ ይሄንን ግንባታ የዘወትር ተግባር በማድረግ መቼም፣ የትም፣ ለምንም ዓይነት ሁኔታ ዝግጁ የሆኑ የጸጥታ ተቋማትን እየገነባን እንድንሄድ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካዊ ኩስመና ባከተመበትና ቁመናዋ እየተስተካለ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ የጸጥታ ተቋሞቻችን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት፣ ዳር ድንበር፣ ሰላምና ደኅንነት፣ ብሎም የብልጽግና ጉዞ ለማስከበር በሚችሉበት ዐቅም እና ዐቋም ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡ ይሄንኑ ወትሮ ዝግጁነት ይበልጥ በማጠናከር፣ የውስጥና የውጭ ችግር ፈጣሪዎችን አደብ አስገዝቶ፣ ሰላምን በሚያጸና ልክ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የጸጥታ ተቋማት ዋና ተልዕኮ ሰላምን ማጽናት ነውና፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም