የታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ የተገነባና የሥራ ባህልን የቀየረ ፕሮጀክት መሆኑን የሠራተኛና አሠሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች ገለጹ

You are currently viewing የታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ የተገነባና የሥራ ባህልን የቀየረ ፕሮጀክት መሆኑን የሠራተኛና አሠሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች ገለጹ

‎AMN ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም

‎ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ የተገነባና የሥራ ባህልን የቀየረ ፕሮጀክት መሆኑን የኢትዮጵያ ሠራተኛና አሠሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች ገለፁ።

‎የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ የህዳሴ ግድብ በርካታ ትምህርቶችን የሰጠ በህብረት የተገነባ የጋራ ፕሮጀክት ነው። ህዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵያዊያን ብርቱ ክንድ የተገነባ መሆኑን አንስተው በተለይ ሠራተኞች ለግድቡ ግንባታ በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበታቸው የበኩላቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል።

‎ግድቡ ቀን ከሌሊት ያለማቋረጥ በመሥራት የተገኘ የትጋት ድል መሆኑን ገልጸው፥ የሥራ ባህልን የቀየረና አንድነታችንን ያረጋገጥንበት የይቻላልና አሸናፊነት ምልክት ነው ብለዋል። ኮንፌዴሬሽኑ ሠራተኛውን በማስተባበር በኩል የሚጠበቅበትን ሚና ሲጫወት መቆየቱንም ነው የተናገሩት።

‎የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጌታሁን ሁሴን(ኢ/ር) በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ በጋራ ተባብረን ከሠራን የምንፈልገውን ግብ ማሳካት እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል። ግድቡ መንግሥት ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር ያሳኩትና ለኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።

‎ኢትዮጵያ ወደፊት ለምትገነባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ትምህርትና ልምድ የተገኘበት መሆኑንም ነው ያብራሩት። የህዳሴ ግድቡ በሁሉም ትብብር የተሠራ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበትና እንደዓይን ብሌናችን የምንጠብቀው ፕሮጀክት ነው ሲሉም ፕሬዚዳንቶቹ ገልጸዋል።

‎በቀጣይ ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች አሠሪዎችንና ሠራተኛውን በማስተባበር ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። የሜጋ ፕሬጀክቶች ግንባታ ከመንግሥት ባሻገር የግሉን ዘርፍና የህብረተሰቡን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ አሠሪዎች ከመንግስት ጎን በመሆን ለሀገር ልማት አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review