የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል ያዘጃጀው የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ነው።
ታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን ተከትሎ በተዘጋጀው በዚህ የፓናል የውይይት መድረክ ላይ ምሁራን፣ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ናቸው።
ውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተቀዳጀነው ድል ወደ ለሌሎች በርካታ ድሎች የሚያረማምደን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ለዘመናት የሀገርን ሀብት ሲያግበሰብስ የቆየው አባይ በህብረትና በአንድነት ሀገር ውስጥ እንዲከትም ሆኗል ሲሉም አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) አክለዋል።
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው፣ ህዳሴ የኢትዮጵያዊያን ቁጭት ተሰብስቦ የተገነባ ግድብ መሆኑን ተናግረዋል።
በፖለቲካዊና መሰል ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ቢኖረንም ህዳሴን እውን ለማድረግ አንድነት የተፈጠረበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአፍሪካ የልህቀት አካዳሚ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ ህዳሴ ግድብ የሚያበራው ጨለማችንን ብቻ ሳይሆን እድል ፈንታችንንም ጭምር ስለመሆኑ አንስተዋል።
የፓናል ውይይቱ ለግማሽ ቀን የሚካሄድ እንደሆነም ተገልጿል።
በበላይሁን ፍስሀ