በዘመን መለወጫ በዓል የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ

You are currently viewing በዘመን መለወጫ በዓል የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ

AMN ነሐሴ 30/2017

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው የዘመን መለወጫ በዓል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ዝግጅት ማድረጉን ገለፀ።

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር በበዓሉ ወቅት ሊከሰት የሚችል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የተደረጉ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም በአዲስ አበባ ከ15 በላይ የዞን ኦፕሬሽን ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀው፤ በክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ የተመሰረተ ግብረ ሀይል ወደ ስራ መገባቱን ነው ያመለከቱት፡፡

አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጀ የኃይል ጫና እና የመስመር እርጅና አለባቸው ተብለው የታሰቡ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮችን በመፈተሽ ማስተካከያ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ37 ሺህ 699 ኃይል ተሸካሚ ትራንስፎርመሮችን በመፈተሽ ማስተካከያ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

አገልግሎቱ በዋዜማና በዘመን መለወጫ ዕለት ሊያጋጥም የሚችለውን የሀይል መቆራረጥ እና መዋዥቅ ለመቀነስ የተለያዮ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በበዓሉ ወቅት የኃይል መቆራረጥ ቢከሰት አስቸኳይ የጥገና ስራ ለማከናወን 24 ሰዓት ምላሽ የሚሰጥ ግብረ ሀይል መዋቀሩን አስታውቀዋል፡፡

ደንበኞች ከፍተኛ ሃይል የሚፈልጉ ተግባራትን የኤሌትሪክ ኃይል ጫና በማይበዛበት በተለይም ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ባሉት ጊዜያት መጠቀም የተሻለ አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ደንበኞችም በበዓሉ ወቅት ሊደርስ የሚችለውን አላስፈላጊ ወረፋ ለመቀነስ ቀድመው ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review