በሩስያ እና ዩክሬን መካከል የሰላም ስምምነት የሚደረስ ከሆነ ለኪየቭ የደህንነት ማስተማመኛ ለመስጠት 26 የአውሮፓ ሀገራት ጦራቸውን ለማሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን ፈረንሳይ ገልጻለች።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑየል ማክሮን የተኩስ አቁም ስምምነቱ በተፈረመ ቅጽበት 26 አጋሮች በአየር ፣ ባህር እና ምድር ጦራቸውን ወደ ዩክሬን ለማሰማራት ሙሉ ፍቃደኛ ናቸው ብለዋል። 35 ሀገራት የተሳተፉበት ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጡት መግለጫ በመጪዎቹ ቀናት የአሜሪካ ግልጽ አቋም ይታወቃል ነው ያሉት።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፣ ሩስያ ጦርነቱን እንድታቆም እና ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንድትገባ የአውሮፓ ህብረት አባላት ከሞስኮ ጋር የሚያደርጉትን የነዳጅ ዘይት ግብይት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
27 አባል ሀገራት ያሉት የአውሮፓ ህብረት በ2027 ከሩስያ ጋር የሚያደርገውን ሁሉንም የጋዝ እና የነዳጅ ምርት ግብይት እንደሚያቆም ሲያስታውቅ፣ ሞስኮ በአንድ አመት ብቻ 1.3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን መረጃዎች ጠቁመዋል።
ሞስኮ የምእራባዊያን ጦር በዩክሬን መሰማራት ጉዳይ ግልጽ አቋሟን አስታውቃለች፤ ይህ አቋሟም ለዩክሬን ደህንነት ማስተማመኛ ለመስጠት ከአንድ ሀገር በላይ እንዲሰማራ አልፈቅድም የሚል ነው።
ምዕራባዊያን የዩክሬን አጋሮች ሁለቱ ተዋጊ ወገኖች ጦርነት ለማቆም የሚስማሙ ከሆነ ዳግም ግጭት እንዳይቀሰቀስ ለመከላከል በዩክሬን ለመሰማራት ጥብቅ መሻት አላቸው።
ሞስኮ በበኩሏ እርምጃው ዳግም የደህንነት ስጋትን የሚፈጥርብኝ ነው በሚል ውሳኔውን አጥብቃ እንደምትቃወም እየገለጸች ትገኛለች።
ይህን ተላልፈው አውሮፓዊያን ወታደሮቻቸውን በዩክሬን የሚያሰማሩ ከሆነ ኢላማ ሊደረጉ እንደሚችሉ ክሪምሊን አስጠንቅቋል።
በዳዊት በሪሁን