የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ለመቀልበስ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተምሳሌት መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ

You are currently viewing የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ለመቀልበስ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተምሳሌት መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ

‎AMN ነሀሴ 30 /2017 ዓ.ም

‎የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ለመቀልበስ፣ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተምሳሌት መሆኗን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልፀዋል።

‎ኢትዮጵያ በየ አመቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በማሳተፍ 48 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል አርአያነቷን ለአለም አሳይታለችም ብለዋል።‎ ‎ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በሁለተኛው የአፍሪካ የወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ነው።

‎ሁለተኛው የአፍሪካ የወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በወጣቶች የሚመራ የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ተጓዳኝ መድረክ ሲሆን በአዲስ አበባ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።

‎በአየር ብክለት ከ4 በመቶ በላይ አስተዋፅኦ የሌላት አፍሪካ በችግሩ የሚደርስባት ጥቃት ግን ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል። ለዚህም የአህጉሪቱ ወጣቶች በልዩ ልዩ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች ገንቢ ውይይቶችን በማካሄድ ለውጥ ለማምጣት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

‎የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ በመቀልበስ ረገድ፣ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተምሳሌት መሆኗን እና ለዚህም የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።‎

በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት ወጣት ተወካዮች ንግግር አድርገዋል፡፡ ወጣቶች በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ቁልፍ የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ መሳተፍና ማቀንቀን እንደሚጠበቅባቸው መልዕክቶች ተላልፈዋል።

‎የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063፣ የአፍሪካ ኅብረት የአየር ንብረት ለውጥ እና የማይበገር ልማት ስትራቴጂዎች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች አካል ነው።

‎የፓሪስ ስምምነት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ብሔራዊ ልማት እቅዶች ሁሉም ወጣቶችን በግንባር ቀደምትነት በማሳተፍ የአህጉሪቷን መፃኢ እድል ብሩህ ማድረግም እንደሚገባቸውም በመድረኩ ተስተጋብቷል።

‎በመድረኩ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶች በሀገሪቱ የወጣቶችን ተሳትፎ አጉልተው አሳይተዋል።

‎ እንደ አረንጓዴ አሻራ ባሉ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን አህጉራዊ ፋይዳቸው ጉልህ በሆኑ ልማቶች የኢትዮጵያ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውም በመድረኩ ተነስቷል።

‎በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review