አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የመዲናዋን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ዉጤታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የመዲናዋን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ዉጤታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

AMN- ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የመዲናዋን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ዉጤታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት እና አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የፊርማ ስነስርዓቱን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ያከናወኑ ሲሆን፤ ስምምነቱ የነዋሪውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ላቅ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አጀንዳ በማደራጀት ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋሙ በአጭር ጊዜ የሚተማመኑበት ተቋም ሆኗል ብለዋል፡፡

ሚዲያ ህዝብ እና መንግስትን የሚያገናኝ ድልድይ ነው በማለት፤ ስምምነቱ የአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት የሚያከናወናቸውን ስራዎች ወደ ህዝብ ለማድረስ ብሎም ህዝብ ጋር ያለውን ሃሳብ ለማድመጥ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ወደ ህዝቡ የሚደርስበት በርካታ ፕላትፎርሞች ያለው መሆኑም ይህንን ለማከናወን ይረዳልም ብለዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፤ ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በከተማዋ ልማት ውስጥ ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ እና የከተማዋን ነዋሪ እርካታ ለማረጋገጥ ይረዳል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከፍ ብላ እድትታይ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት አበርክቶ ላቅ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን ስራዎችም ማሳየት እንደሚገባ እና በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኃላፊነት ጉልህ መሆኑን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአቀራረብ እና ይዘት ተመራጭ እና ተወዳዳሪ ሆኗል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ተቋሙ ትክክለኛ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ የመሆን ግቡን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በመንግስት እና ህዝብ መካከል ድልድይ በመሆን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ብልሹ አሰራሮች እዲጋለጡ የማድረግ እና ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር በአግባቡ እንዲያገኝ በማድረግ ተግባር ውስጥ በስፋት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

ኤ ኤም ኤን በቴክኖሎጂ እራሱን በማደራጀት፣ ብዝሃነትን በማስረጽ በተለያዩ ቋንቋዎች ህዝቡ ጋር እየደረሰ ያለ ተቋም መሆኑን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በአሁኑ ወቅት በ5 የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እና ሁለት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በድምሩ በ7 ቋንቋዎች በተለያዩ አማራጮች ህዝብ ጋር እየደረሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመሆን ለተሻለ ነገር እንደሚሰሩም አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review