ለ16 ዓመታት በሕመም ፍቃድ ላይ የቆየችው መምህርት የህመሟን ማስረጃ እንድታቀርብ በመጠየቋ አሠሪዋን ከሰሰች

You are currently viewing ለ16 ዓመታት በሕመም ፍቃድ ላይ የቆየችው መምህርት የህመሟን ማስረጃ እንድታቀርብ በመጠየቋ አሠሪዋን ከሰሰች

AMN – ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም

ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ ሙሉ ደሞዟን እየተቀበለች ለ16 ዓመታት በህመም ፍቃድ ላይ የቆየች አንዲት ጀርመናዊት መምህርት፣ የጤና ሁኔታዋን ለማረጋገጥ የህክምና ምርመራ እንድታደርግ መጠየቋን ተከትሎ በአሠሪዋ ላይ ክስ መስርታለች።

በስም ያልተጠቀሰችው መምህርት በአሠሪዋ ላይ ክስ የመሰረተችው፣ ባልተለመደ መልኩ ለረጅም ጊዜ ከሥራ መቅረቷ ያጠራጠረው መሥሪያ ቤቷ የህክምና ምርመራ እንዲደረግላት በመጠየቁ መሆኑ ተገልጿል።

ለ16 ዓመታት በህመም ፍቃድ ላይ የነበረችው መምህርት፣ በዚህ ሁሉ ዓመት ውስጥ በምትሰራበት በቬዘል በሚገኝ አንድ የሙያ ኮሌጅ ውስጥ ግዴታዋን ሳትወጣ ነገር ግን ሙሉ ደሞዟን ስትቀበል መቆየቷ ተነግሯል፡፡

በጀርመን ሕግ መሠረት መምህራን ላልተወሰነ የህመም ፍቃድ በሚወጡበት ጊዜ ሙሉ ደመወዛቸውን መቀበልን ጨምሮ አንዳንድ ጥቅሞች ያስገኝላቸዋል።

እንደ ኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ከሆነ፤ በሰሜን ራይን-ዌስትፋሊያ የሚገኙ መምህራን በየወሩ እስከ 7 ሺህ 200 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ይችላሉ።

ታዲያ መምህሯ በየዓመቱ 84 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የምታገኝ ሲሆን፤ በዚህም በአጠቃላይ ከ16 ዓመታት በላይ በሕመም ፍቃድ ላይ እያለች 1 ሚሊየን 166 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገደማ አግኝታለች።

ይህ ያልተለመደ ጉዳይ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በትምህርት ቤቱ አመራር ለውጥ ምክንያት ተገኝቷል፡፡

የትምህርት ቤቱ የበላይ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የውስጥ ምርመራ፣ በየወሩ የህክምና ምስክር ወረቀት ስታቀርብ እንደነበር ቢገልፅም፣ የጤናዋ ሁኔታ ግን በህክምና ባለሙያ አልታየም ነበር።

በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ የመምህሯ አሠሪ የጤንነቷ ሁኔታ እንዲረጋገጥ እና የሕክምና ምርመራ እንዲያደርግላት በመፈለግ የጠየቀው።

ይሁን እንጂ መምህሯ የጤና ምርመራ በማድረግ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አሰሪዋ ላይ ክስ የመሰረተች ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ክሷን ውድቅ አድርጎታል፡፡

አሰሪዋም የጤና ማረጋገጫ የመጠየቅ ሙሉ መብት እንዳለው አረጋግጧል፡፡

በጀርመን ህግ መሰረት አንድ አስተማሪ በህመም ፍቃድ ላይ ከሆነ በሌላ የማይተካ ሲሆን፣ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡

መምህሯ የፈጸመችው ተግባር ከባድ የህግ ጥሰት በመሆኑ፤ ሥራዋን፣ ደሞዟን እና የጡረታ ጥቅሟን ጭምር ሊያስቀር እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የህግ ባለሙያው ራልፍ ዴልግማን እንደገለጹት፣ የዚህ ያልተለመደ ጉዳይ ውጤት በህክምና ምርመራ ውጤት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡

ነገረ ግን ከሥራ በቀረችባቸው 16 ዓመታት ታማ ይሁን አይሁን በትክክል ለማወቅ ለሚመረምራት አካል አዳጋች ስለሚሆን በዛን ወቅት የወሰደችውን ደሞዝ መመለስ እንደማይጠበቅባት ነው የተገለጸው፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review