የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለሠራተኞችና በጡረታ ለተሰናበቱ የቀድሞ አባላቱ ማዕድ አጋርቷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው፥ጳጉሜን 2 2017 ዓ.ም የሚከበረውን የህብር ቀንና አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሠራተኞችና በጡረታ ለተሰናበቱ የቀድሞ አባላት የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር ተከናውኗል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ለበአል መዋያ የሚሆን የቁሳቁስ ሥጦታና የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቷል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ርስቱ ይርዳው፥ ትናንት ሀገራቸውንና ተቋማቸውን በትጋትና ዋጋ በመክፈል ጭምር ያገለገሉትንና ዛሬም እያገለገሉ የሚገኙትን ሠራተኞች መደገፍ በሀገር ደረጃ የተጀመረው የሰው ተኮር ልማት ሥራችን አካል ነው ብለዋል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተጣለበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ለተለያዩ የኅበረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ርስቱ፥ በዛሬው ዕለት የተደረገው የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብርም የዚሁ ተግባር አካል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የተቋሙ ሠራተኞች ከወር ደመዛቸው በማዋጣት አቅመ ደካማና አረጋውያን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ርስቱ፤ ይህም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን ከማኅበረሰቡ ጋር ይበልጥ ማስተሳሰሩንና ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ እድል መፍጠሩን አመልክተዋል።
በቀጣይም የማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፥ በተቋም ደረጃ የተሰጠንን ተልዕኮ ከመፈጸም ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የማኅበረሰብ ተኮር የድጋፍ ሥራዎች ላይ ያለን ተሳትፎ እያደገና ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ወረዳ የመሬት መንሸራተት ላጋጠማቸው ዜጎች እና ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ ከማድረጉ ባሻገር የተቋሙ ሠራተኞችና የአረጋውያንን መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን በማደስና በመገንባት በኩል ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን አገልግሎቱ ለኢዜአ የላከው መረጃ ጠቁሟል፡፡