የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጽናት ቀንን ስናከብር ለሀገራችን እና ለከተማችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እንደ ከዚህ ቀደሙ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ያለንን የማይናወጥ ጽናት ዳግም በማረጋገጥ መሆን ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ጳጉሜ 1፣2017 “ጽኑ መሰረት ብርቱ ሀገር” በሚል አገራዊ መሪ ቃል የጽናት ቀን እንደሚከበር ገልጸዋል።
መሪ ቃሉ በጽናት ላይ የተገነባ ሀገር ጠንካራ እና ለየትኛውም ጊዜያዊ ፈተና የማይበገር ፣ እጅ የማይሰጥ በመጨረሻም ድል አድራጊ መሆኑን ያሳያል። ፅናት ለእኛ ኢትዮዽያውያን እንደ ቡናችን ፣ እንደ አባይ ወንዛችን አንዱ መገለጫችን ነው። በጦርነት አዉድማ ቀደምቶቻችን በአድዋ ፣ በማይጨው፣ አትሌቶቻችን ደግም በስፓርት ሜዳ ፅናትን አሳይተውናል ብለዋል።
የቅርቡን እንኳን ብንመለከት በህዳሴ ግድባችን የባዳና ባንዳው ጥምረት እንዳለ ሆኖ ለ 13 ጊዜ ያህል በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ስንሆን ፣ ከዉስጥም ከዉጪም የተቀናጁ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ዛሬ ግድባችንን ጨርሰን የደረስንበት የታሪክ እጥፋት ከመሪ እስከ ህዝብ ያለንን ፅናት ለዓለም ህዝብ ያሳየንበት ነው። በስንዴ አብዮት ፣ በአረንጓዴ አሻራ ጭምር የስኬታችን ዋነኛው ሚስጥር የመሪዎቻችንና መሪውን የተከተለዉ ህዝብ ፅናት ነው ።

በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ ከተማ ያለማቋረጥ ወደፊት ይገሰግሳል ፤ የትኛዉም ምድራዊ ሀይል ካለመበት አያስቀረውም፣ በአዲስ ሀይል አዳዲስ ስኬቶችን ይጨብጣል ብለዋል። በከተማችን በ2017 ዓ.ም የታየው ፣ ዓለምን ያስደነቀው ፣ አዲስ አበባን አዲስ እና አበባ ያደረገው ስር ነቀል መልሶ ማልማት ፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፣ የገቢ አሰባሰብ ፣ የሰላምና ፀጥታ ወዘተ በርካታ ተግባራት ፣ እንዲሁ በቀላሉ የተገኘ ውጤት አይደለም፤ ይልቁኑ በፅናት በመጓዝ የተገኘ እንጂ።
ፈተና ሳይኖር ቀርቶ አይደለም ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የከተማችን ነዋሪ ተሳትፎ ፣ በፅናት የተቀናጀ የአመራር ሰጪነት የታየበት ተጨባጭ ውጤት ፣ የጠንካራ ፅናታችን ውጤት በመሆኑ በአዲሱ የ2018 ዓመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በዛሬዉ እለት የጽናት ቀንን ስናከብርም ለሀገራችን እና ለከተማችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እንደ ከዚህ ቀደሙ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ያለንን የማይናወጥ ጽናት ዳግም በማረጋገጥ መሆን ይኖርበታል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።