የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው፣ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው ረገድ ከቀድሞው የተለየ አቅም እንደሚያጎናጽፋት ተመላክቷል
ዓለማችንን እንዳሻቸው የሚዘውሩ ሀገራት፣ ምድራችን እየተናጠችበት ያለው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና መሰል ጉዳዮች ዋና ምስጢር ኢኮኖሚ ነው። ለዚህ ደግሞ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፖለቲክስ፣ የጂኦ ኢኮኖሚክስ እና የቴክኖሎጂ ማዕከል ተመራማሪ ማርከስ ጄገር (ዶ/ር) እ.ኤ.አ ግንቦት 2022 በዓለም ላይ ሁለንተናዊ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት አቅምን በኢኮኖሚ ማፈርጠም ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ለጀርመን የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ያቀረቡትን ጥናታዊ ፅሑፍ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
እንደ ማርከስ ጄገር (ዶ/ር) ምልከታ የኢኮኖሚ አቅም የፖለቲካ እና የወታደራዊ ኃይል መሰረት ነው። በኢኮኖሚ ምንም ከሆንክ በዳቦ ጠቅልለው የሰጡህን ፖሊሲ እና አጀንዳ ከማስፈፀም ውጭ ምንም ማድረግ አትችልም፡፡ እናም ኢኮኖሚ በተሳካ የረጅም ጊዜ ጂኦ ፖለቲካዊ ውድድር ውስጥ ለመሳተፍም ቅድመ ሁኔታ ነው።
በኢኮኖሚ ፈርጣማ የሆኑ ሀገራት በፀጥታው ምክር ቤት፣ በዓለማችን ትልልቅ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና መሰል ተቋማት ላይ ያላቸውን የመወሰን አቅም መመልከት በቂ እንደሆነም ማርከስ ጄገር (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ በኋላ በብዙ መስፈርቶች ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ እንደሚጨምር መረዳት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴው ግድብ ለፍሬ መብቃቱን አስመልክቶ “የኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ ከግድቡ በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ እና ከግድቡ በኋላ የምትኖረው ኢትዮጵያ የተለያዩ ናቸው ማለታቸውንም በዋቢነት መጥቀስ እንችላለን፡፡
ለብዙ ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያውያን ጥያቄ የሆነው የህዳሴ ግድብ መጠናቀቁ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲካው መስክ ያላትን ተሰሚነት አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በርካታ አንድምታዎችን የሚያመጣ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመጀመሪያው ግድቡ የጎንዩሽ ጉዳት ያመጣብናል ብለው ለሚያስቡት አካላት መልስ የሚሰጥና ግድቡ ተጠናቅቆ ያመጣው አንዳችም ተጽዕኖ እንደሌለ የሚያረጋግጥ ነው። በሌላ በኩልም ከተለያዩ አካላት ተልዕኮ ወስደው ሲሰሩ ለነበሩ አካላት መልስ የሚሰጥ እና የኢትዮጵያውያን አንድነት ምን ያህል እንደሆነ ያሳየንበት ነው። በመሆኑም በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ የህዳሴ አይነት በርካታ ፕሮጀክቶችን ጀምራ ታጠናቅቃለች ብለዋል፡፡
ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው በበኩላቸው፣ ያደጉ ሀገራት በታላላቅ መድረኮች ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን አጀንዳ በሌሎች ላይ የሚጭኑበት ምስጢር አንዱና ዋናው የኢኮኖሚ አቅም መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ኢኮኖሚና የኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ ያላቸው ትስስር ከፍ ያለ ነው፡፡ እናም እንደ ሀገር በኢኮኖሚ ከፍ ብሎ ለመታየት ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ኃይል ግድ ይላል፡፡ የኤሌክትሪክ ተፅዕኖ በዓለም የኢኮኖሚ እድገት ላይ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ነሐሴ 27 ቀን 2020 በሪሰርች ጌት ላይ የታተመ ጥናታዊ ፅሑፍ እንደሚጠቁመው ብዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረትና መጠቀም የቻሉ አሜሪካና ቻይናን የመሳሰሉ የዓለማችን ሀገራት አድገዋል፡፡ ያልቻሉት ደግሞ እንደ ተቀባይ እጅ ዝቅ ብለው የሰጧቸውን ብቻ አሜን ብለው በድህነት አዘቅት ለመኖር እንደተገደዱ በጥናታዊ ፅሑፉ ሰፍሯል፡፡
ጥናቱ በመቀጠል ቀላል የማይባሉ የአፍሪካ ሀገራት በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሌላቸው በኢኮኖሚ ከፍ ማለት አልቻሉም፡፡ ከዚህ ጥናታዊ ፅሑፍ መደምደሚያ ሀሳብ መረዳት እንደሚቻለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ አቅም መጎልበት የሚኖረው ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን ነው፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ይንገስ ዓለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉትም ኤሌክትሪክ ኢንዱስትሪን ከፍ በማድረግና በማስፋፋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ እድገትን በማጎልበት እና አጠቃላይ የኑሮ ደረጃን በማሻሻል ለሀገር ብልጽግና ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የሀገር ኢኮኖሚያዊ አውታሮች በብቃት እንዲንቀሳቀሱ፣ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን በመፍጠር ድህነትን ይቀንሳል፣ ኢንቨስትመንትን ይስባል፣ ይህ ሁሉ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል። በመሆኑም የህዳሴው ግድብ በኢኮኖሚው የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያግዛልም ብለዋል፡፡
የዓለም ኃያላን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በዓለም አቀፍ ንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በፋይናንሺያል ገበያ እና በቴክኖሎጂ ልማት ላይ ባላቸው ከፍተኛ ተፅዕኖ እና የዓለም አቅርቦት ሰንሰለትን እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ በኩል በጉልህ እንደሚታይ የጠቆሙት በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው፣ ኢትዮጵያ በራስ አቅም እውን ያደረገችው የህዳሴው ግድብ ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁለንተናዊ መልኩ ተወዳዳሪ እና አሸናፊ የሚያደርጋት ነው፡፡
የኢኮኖሚ ኃይል ለሀገራት ደኅንነት፣ መረጋጋት እና ለጠንካራ የመከላከያ ኃይል፣ የዜጎችን ሕይወት እንዲያሻሽል እና ለሌሎች ሀገራት ጭምር በመትረፍ ትብብር እንዲፈጠር ያደርጋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምታገኘው ኃይል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሚገባ በማንቀሳቀስ ትልቅ ድል የሚያመጣ ነው፡፡
እንደ ፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ገለፃ፣ የህዳሴው ግድብ በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትግልና ጥበብ የተገኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ብቻ በተደጋጋሚ በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ የሆነችበት፣ ለሌሎች ሀገራት የሰራው ዓለም አቀፍ ሕግ ™በራስ ሀብት የመጠቀም መብት∫ ሚዛኑ ተንሻፍፎ የታየበት እና መሰል ጫናዎች የተደረጉባቸው መድረኮች የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው፡፡ ግን ይህንን ሁሉ በጥበብ እና በእውነት አሸንፈን ወጥተናል፡፡ ይህም ድል ከዓድዋ ድል ቀጥሎ ያገኘነው የዘመናችን ገድል ነው። በመሆኑም የህዳሴው ግድብ ስኬት ኢትዮጵያ ልክ እንደ ዓድዋ ድል በአፍሪካ ብሎም በዓለም የታሪክ መድረክ ላይ የምትፈራና የምትከበር ሀገር መሆኗን የመሰከረችበትም ደማቅ ታሪክ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አክለውም፣ የህዳሴው ግድብ ስኬት ከጥንት እስከ ትናንት በሚታይም ሆነ በማይታይ መልኩ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል፣ በማጋጨት እና ጥቅሟን አሳጥቶ ልማት ላይ እንዳታተኩር በማድረግ ሲያሴሩባት የነበሩ ኃይሎችን ቅስም የሚሰብር እና ዳግም በክፉ እንዳይመለከቷት ትምህርት የሚሰጥ፣ በአንፃሩ ደግሞ ሀገር ከዘመናት ቀንበር ተላቅቃ በዓለም አደባባይ ቀና ብላ የምትጓዝበትን ዕድልና አቅም የሚፈጥር ዘመንን በበጎ የከፈለ የጋራ ድል ነው ብለዋል፡፡
ከእንግዲህ ኢትዮጵያን ማንም በክፉ እንዳያስባት ቢያስባትም ሊያሸንፋት እንደማይችል የህዳሴው ግድብ ቋሚ ምስክር ነው፡፡ አፍሪካ ላይ ለሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ምክር የምትጠየቅ ሀገር፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምታቀርባቸው ሀሳቦች የበለጠ ተቀባይነታቸው ከፍ ያለላት እንዲሁም ለአንድ ዓላማ በጋራ ተነስተው ማሳካት የሚችሉ ህዝቦች ያሉባት ሀገር መሆኗን ልክ እንደ ዓድዋ ድል ዳግም የሚመሰክር ነው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ይገኛል። የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደምትችል የሚያሳይ ነውም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከምናየው እና ከምንሻው የሩቁ ህልማችን ላይ ዐይናችን ሳይነቀል ተግተን በተደመረ አቅም ከተሰራ የኢትዮጵያን ብልጽግና ባጠረ ጊዜ ማሳካት እንደሚቻልም መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
እናም በተባበረ ክንድ በዓባይ ወንዝ ላይ ያስመዘገብነው ድል ትናንት…
“በችጋር በጠኔ፣ በረሃብ ብንማቅቅ፣
ምኑ ነው የሚደንቅ!
አብሮ መብላት እንጂ፣ አብሮ መሥራት አናውቅ!” ይሉትን አባባል ፉርሽ አድርጎ እንደ ሀገር በጋራ የምንቆም፣ ቆመንም ድል የምናደርግ የአፍሪካ ብልፅግና ተምሳሌቶች መሆናችንን የሚመሰክር እንደ ሐይቁ ስያሜም ንጋታችንን የሚያሳይ የዘመናችን ታላቅ ድል ነው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡፡
በመለሰ ተሰጋ
#GERD
#Ethiopia
#Development
#Economy
#Politics
#Deplomacy