የብዝሃነት እልፍኝ

You are currently viewing የብዝሃነት እልፍኝ

አዲስ አበባ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን የመቻቻል ተምሳሌት መሆኗ ተገልጿል

አዲስ አበባ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት።  የመንግሥት መናገሻና የሀገሪቷ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ማዕከል መሆኗ ለዚህ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆን ባለፈም የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎችም በብዛት ይገኙባታል። ይህም  በርካታ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የውጭ ዜጎች የሚንቀሳቀሱባት፣ ውለው የሚያድሩባት እና የሚኖሩባት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የብዝሀ ኃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና ብሔር መናገሻም ናት።  እነዚህ ሁሉ ተደማምረው አሁን ላይ ከተማዋ የብዝሃነት ማዕከል እንድትሆን አስችለዋታል።

ሌላውን ትተን የአዲስ አበባ አንድ አካል የሆነውን መርካቶን ብንመለከት፤ በመዲናዋ ያለውን የብዝሃነት መልክና ውበት እንረዳዋለን፡፡ በመርካቶ በንግድ ሥራ የተሰማሩት የከተማ ነዋሪዎች ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ ታታሪ ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነሱ ገዝተው ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ምርቶችን የሚያደርሱ በርካታ አነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እንደዚሁ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ የተለያየ ማንነት ያላቸው ሰዎች በመርካቶ ማዕከልነት፣ በንግድ ሥራ አስተሳሳሪነት ብዝሃነታቸው ሳይገድባቸው የሰመረ መስተጋብር ያደርጋሉ፡፡ ግንኙነታቸው ከንግድ ባሻገር በፍቅርና ወዳጅነት ደርጅቶ ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያድግበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነ እሙን ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህልና የሰላም ተመራመሪ ወሰን ባዩ (ዶ/ር) ስለአዲስ አበባ ህብርነት ሲያብራሩ፤ “መገለጫዎቹ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ማህበራዊ ጉዳይን ብንወስድ አዲስ አበባ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ መጠን የየራሳቸው ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ አላቸው፡፡ ይህም በራሱ የሚፈጥረው የእርስ በእርስ ማህበራዊ መስተጋብር አለ፡፡ ማህበራዊ መስተጋብሩም አዲስ አበባን እንደ ስሟ በብዝሀ ባህልና ማንነት አብባና ደምቃ እንድትታይ አድርጓታል” ብለዋል፡፡

በመዲናዋ ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንጻር ምን ተሠራ?

የህብር ማሳያ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንጻር የተሠሩ ሥራዎች የእርስ በእርስ ትውውቅን ለማጎልበትና ወንድማማችነትን ለማጠንከር እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ እንዲሁም ቀጣይ ምን ለመሥራት እንደታሰበ የዝግጅት ክፍላችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ፤ የባህል እሴቶች ልማት ቡድን መሪ አቶ አንሙት ከልካይን አነጋግሯል። እሳቸው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንደጠቆሙት፤ በተቋሙ ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንጻር የተለያዩ  ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠበቅ እና በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል። ጠቃሚ የባህል እሴቶቻችንና ሀገር በቀል እውቀቶቻችንን በመለየት ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጠቀሜታ የሚውሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የክብረ በዓላትን እና የፌስቲቫሎችን ሁነት በማዘጋጀት ማህበረሰባዊ ትስስርን እና አንድነትን ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

“ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የተለያየ መሪ ሀሳብ በመጠቀም ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫሎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በየዓመቱም ቶክ ሾው እና አውደ ርዕይ በማዘጋጀት፣ በተለያዩ ዘርፎች የባህል ውድድሮችን እና ልዩ ልዩ ሀገረሰባዊ ጨዋታዎችን በክፍለ ከተሞች፣ በባህል ተቋማት፣ በእደ ጥበብ ተቋማት፣ ማህበራትና ግለሰቦች መካከል ተካሂዷል፡፡ አሸናፊ ለሆኑት ዕውቅና እና ሽልማት በመስጠት በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ኃይማኖቶች መካከል ያለውን የመቻቻልና የመከባበር እሴት ለማጠናከር ጥረት ተደርጓል፡፡ የባህል ሙያ ምርት ውጤቶችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በማካሄድ የማስተዋወቅ፣ ልዩ ልዩ ማህበረ ባህላዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ የባህል ክዋኔ ትርኢቶችን እንዲሁም ርእሰ ጉዳዩን የሚመለከቱ ህዝባዊ ዘፈኖችና ሀገረሰባዊ ትርኢቶች የክዋኔ አውዱን በጠበቀ መልኩ እንዲቀርቡ ተደርጓል። የብዝሃ ማንነት ማሳያ በሆነችው አዲስ አበባ የሚዘወተሩ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦችን፣ የመመገቢያ ቁሶቻቸውንና ምግቦቹ የሚቀርቡበት ማህበረ ባህላዊ አጋጣሚና የየማህበረሰቡ ወግና ሥርዓት የሚያስተላልፉ ክዋኔዎች ተዘጋጅተዋል፡፡

በሌላ በኩል የቡሄ በዓል፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን፣ የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን እና ሚያዝያ 27 የድል ቀን በዓላትን በየዓመቱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንዲከበሩ መደረጉን የጠቆሙት የባህል እሴቶች ልማት ቡድን መሪ አቶ አንሙት፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን፣ የኢሬቻን እና  የአሸንዳ፣ የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ጎቤና ሽኖዬ በዓላት በተለያዩ ዝግጅቶች መከበራቸውን አብራርተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በጠቃሚ ባህላዊ እሴቶች፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ማህበራዊ ተቋማት ልማትና ፋይዳ እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ላይ 30 የተለያዩ የስርፀት ሥራዎች ተከናውነዋል። ከዚህ አንፃር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትንና የዘርፉን ምሁራንን በማሳተፍ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የባህልና ቋንቋ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የሚቀርቡበት ከተማ አቀፍ የባህልና ቋንቋ ጉባኤ የማዘጋጀት ሥራ ተጀምሯል፡፡

የቋንቋ ልማት እና አጠቃቀም የማጎልበት ሥራን በተመለከተ አቶ አንሙት በሰጡት ሀሳብ፤  በቋንቋ ልማት ሥራዎች አና በቋንቋ ፖሊሲ ትውውቅ ላይ ለዘርፉና ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ዓለም አቀፍ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመናገር ቀንን እና በቋንቋ፣ በምልክት ቋንቋና ትርጉም ከተማ አቀፍ ጉባኤዎችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በተለያዩ መሪ ሀሳቦችና ርዕሶች የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ክፍለ ከተሞች እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተገኙበት ጉባኤ እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡

የማህበረሰቡ ባህልና ወጎች መተዋወቃቸው ያስገኘው ፋይዳ

እንደ አቶ አንሙት ማብራሪያ ከሆነ፤ በየዓመቱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የጋራ

የሆኑት በዓላት እንዲከበሩ እና እንዲለሙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህ መደረጉ ለከተማዋ  ገፅታ ግንባታ ጉልህ አስተዋጾኦ አበርክቷል። የብዝሀ ባህል አካታችነትን በማጎልበት ማህበራዊ ትስስርን አጠናክሯል፡፡ ክብረ በዓላቱ የህዝቦች የአብሮነትና የአንድነት ማጠንከሪያ፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ማሳያ፣ የማህበረሰብ የእርስ በርስ የባህል ልውውጥ እና ትውውቅ መፍጠሪያ አጋጣሚ መሆን ችለዋል፡፡ የማህበራዊ ማንነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊ አልባሳት፣ መዋቢያዎች፣ ምግብና መጠጦች በሰፊው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ሰፊ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማሳደግ አስችሏል፡፡

“በማህበረሰቡ መካከል የእርስ በርዕስ ትውውቅ፣ የባህል ልውውጥ፣ ትብብርና ግንኙነት እንዲፈጠር ክብረ በዓላትና ፌስቲቫሎች እንደ ከተማ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ የተፈጥሮን ዑደት በመዘከርና በህያውነት ለማሻገር የሚረዱ ትዕምርታዊ ወይንም ምልክታዊ መገለጫ ሆነው የትናንትን ታሪክ ለዛሬው ትውልድ የሚያደርሱ ድልድዮች ናቸው፡፡ እነዚህም ለሕዝብ አንድነት፣ ለሀገር ገፅታ ግንባታ እና ለኢኮኖሚው እድገትም ወሳኝ መሆኑን አቶ አንሙት አስረድተዋል፡፡

የባህል ፌስቲቫል መካሄዱ፤ የከተማዋን ባህላዊ እሴቶችና ትውፊታዊ (ፎክሎር) ሀብቶች ወይንም ሀገር በቀል እውቀቶች እንዲተዋወቁ፣ እንዲጠበቁና ለስብዕና እና ለገፅታ ግንባታ እንዲውሉ አግዟል፡፡ የየማህበረሰቡ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ፣ ቃላዊና ክውን ጥበባዊ ባህሎችና ልማዶች በአንድ ቦታ እንዲከወኑ፣ ሲምፖዚየሞችና የባህል አልባሳት የዲዛይን ውድድሮች እንዲካሄዱ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በዚህም

በከተማዋ የሚኖሩ ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ትውውቅ እንዲፈጥሩ፣ ተግባቦትና ትስስራቸው እንዲጠናከር መልካም አጋጣሚን አስገኝቷል። አገረሰባዊ እደ ጥበብ ምርቶችን ከማምረት እስከ መጠቀም የሚኖረውን ሂደት አስተማሪ በሆነ መልኩ ለማሳየት እንዲሁም ምርቶቹ የየትኛው አካባቢ ማህበረሰብ መገለጫ እንደሆኑ ለማስረዳት አግዟል። ከዚህም በተጨማሪ የአንደኛው ባህል ባለቤት ከሌለኛው እንዲማር፣ እንዲገዛ፣ እንዲያደንቅ፣ እውቅና እንዲሰጥ… በሂደትም የህብረ ብሔራዊነት አንድነት እንዲገነባ መደላድል ፈጥሯል፡፡

ተመራመሪው ወሰን ባዩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከተማዋ በብዝሀ ባህልና  ማንነት አብባና ደምቃ መገኘቷ የቱሪዝም መዳረሻነቷን የበለጠ እንደሚያሳድገው እና በተለይም ለኮንፈረስ ቱሪዝም ተመራጭነቷን እያሳደገው እንደሚሄድ ነው የሚናገሩት፡፡ የተለያዩ ማንነት፣ ወግ፣ ባህል፣ ስርዓት መኖሩ በራሱ ከተማዋ እንደ መዲና የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ እንድትሆን አስችሏል፡፡ ከእውቀትና ከስልጣኔ አንጻርም ብሔር ብሔረሰቦቹ የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ለምሳሌ የጉራጌ ማህበረሰብ ጠንካራ የስራ ባህልን መውሰድ ይቻላል፡፡ መቻቻል የሚገለጸው በብዝሃ ማህበረሰብ ውስጥ ከመሆኑ አንጻር አዲስ አበባ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን የመቻቻል ተምሳሌት መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡

ህብረ ብሔራዊ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምን መሠራት አለበት?

እንደ ተመራማሪው ወሰን ባዩ (ዶ/ር) ገለጻ፤ አዲስ አበባ ህብራዊነቷ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በርካታ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንደኛው መንግስት ሲሆን ብሔር ብሔረሰቦቹ የማንነት መገለጫዎቻቸውን አጉልተው የሚያሳዩበትን የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀት ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ስራዎችን መስራት አለባቸው፡፡

ነዋሪዎችም በልዩነት ውስጥ አንድነታቸውን በማጉላት የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህላቸውን የበለጠ ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡ “እርስ በእርስ በመረዳዳትና በያገባኛል ስሜት እየኖርኩባት ነው፤ እየሰራሁባት፤ እየነገድኩባት ነው” የሚለውን አስተሳሰብ በማንገብ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የከተማዋ ህብረ ብሔራዊነት እንዲጠናከር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መስራት አለባቸው፡፡ የሚዲያና የእምነት ተቋማትም ድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡    

  በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review