ግድቡ የአሁኑ ትውልድ የአያት፣ ቅድመ አያቶቹን ጀግንነት፣ አልበገርምባይነትና ፅናት በልማት የደገመበት ታላቅ ስራ መሆኑ ተገልጿል
***********************************************************************************
ኢትዮጵያ ባለብዙ ታሪክ ሀገር ናት። በዓለም ላይ ረጅም ስርዓተ መንግስት ካላቸው ጥቂት የዓለም ሀገራትም አንዷ ናት፡፡ በተለያዩ ዘመናት ያጋጠማትን የውጭ ወረራ መክቶ ሉዓላዊነቷንና ነፃነቷን በማስጠበቅ፣ በሰው ዘር መገኛነቷ፣ በበርካታ የታሪክና ቅርስ ሀብቷ፣ በብዝሃነቷ፣ ልዩ በሆነው የዘመን አቆጣጠር ቀመሯና በሌሎችም ትታወቃለች፡፡
ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባለው የአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ፣ የዓባይ ውሃ ምንጭና ለቀይ ባህር ቅርብ የሆነች ሀገር ከመሆኗ የተነሳ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የህልውና እና ደህንነት አደጋ ሲያጋጥማት እንደቆየ “የሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” በሚል ርዕስ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው ሰነድና የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ኑሩ ይማም ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ከውስጥና ከውጭ ሉዓላዊነቷንና ህልውናዋን የሚፈታተኑ ችግሮች ሲያጋጥሟት ኖረዋል፡፡ መቶ እና ሁለት መቶ ዓመታት ወደኋላ ብንመለስ ግብፆችን፣ ደርቡሾችን፣ ጣሊያኖችን ጣሊያኖችን እና እንግሊዞችን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ሀይሎች ኢትዮጵያን በሀይልና በተለያየ መንገድ በመያዝ በተፅዕኗቸው ስር ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን በውስጥ ልዩነት ቢኖር እንኳን እሱን ወደ ጎን ትቶ በአንድነትና በጋራ ቆሞ ወረራዎችን በመመከት የሀገርን ሉዓላዊነትና ነፃነት ተጠብቆ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነቷ ተከብሮና ታፍሮ እንዲቀጥል ከማስቻሏም ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረክ ባላት ንቁ ተሳትፎ እንደምትታወቅ የኢትዮጵያና የአረቡ ዓለም ግንኙነት የታሪክ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለዝግጅት ክፍላችን ይናገራሉ፡፡ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ የዓለም መንግስታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ሲመሰረት ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የአፍሪካ አባል ሀገር ነበረች፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1945 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲመሰረት ከመስራቾች መካከል አንዷ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት ለነፃነታቸው የሚያደርጉትን ትግል በመደገፍ እንዲሁም ነፃ ከወጡ በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (የአሁኑን የአፍሪካ ህብረት) በመመስረት ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች፡፡
በጀግንነት፣ በአልበገርባይነት፣ በፅናት በመቆም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ አኩሪ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ሀገር ብትሆንም፤ ደማቅ የሆነው ታሪኳን ድህነትን በማጥፋት አለመድገሟ፤ በርካቶች አጥንታቸውን የከሰከሱለት፤ ደማቸውን ያፈሰሱለት ዓላማ ሙሉ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡
እንደ ዓባይ ያሉ ወንዞች ቢኖሯትም አልምታ መጠቀም ባለመቻሏ በተለያዩ ጊዜያት ለአስከፊ ረሃብ ተጋላጭ አድርጓት ቆይቷል፡፡ የጥቁር ዓባይ መፍለቂያ ሆና ዜጎቿ በውሃ ጥም በማለቃቸው “የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው” እየተባለ መተረቻ እስከመሆንም ደርሳለች፡፡
ጊዜው ደርሶ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ሲጣል፤ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ የመስራት የዘመናት እንቆቅልሽ መፈታት ጀመረ። የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ ዓባይን የሚያክል ውሃ ቢኖራትም አልምታ መጠቀም ባለመቻሏ በተለያዩ ጊዜያት በድርቅና በረሃብ አለንጋ ስትቀጣ ኖራለች፡፡ ዓባይ ወደታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ውሃ ብቻ ሳይሆን ጥቁርና ቀይ አፈር እንዲሁም ማዕድናትን ጭምር ነበር ይዞ ሲሄድ የነበረው፡፡ ውሃ እያላት በድህነት ውስጥ መኖሯ ቁጭት ፈጥሮ፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ገንብታለች፡፡
የዘመናት ቁጭት መፍቻ የሆነውን ግድብ ግንባታ እውን ማድረግ ሲጀመር ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ደስታቸውን በሰልፍና በተለያዩ መድረኮች ገልጸዋል፡፡ ህጻናት ለብስኩትና ከረሜላ ከሚሰጣቸው፣ እናቶች መቀነታቸውን እየፈቱ፣ ሰራተኛው ከደመወዙ፣ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ገንዘቡን ብቻም ሳይሆን ምርቱንና እንስሳቱን በዓይነት በመስጠት፣ ነጋዴው ማህበረሰብ ገንዘብ በማዋጣት፣ ቦንድ በመግዛት፣ በስጦታ፣ በቁሳቁስ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዕውቀት… ሁሉም ያለምንም ልዩነት እጁን ዘርግቷል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ገባር ወንዞች ሲገናኙ ትልቁንና ሀይለኛውን የዓባይ ወንዝ እንደሚፈጥሩ ሁሉ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዓባይ ልጅነት ጥላ ስር ለአንድ ዓላማ ተሰባሰቡ፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የህዝብና የመንግስት ድጋፍ ያልተለየው ሲሆን ሂደቱ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ከውስጥም ከውጭም ፈታኝና ውስብስብ ፈተናዎች አጋጥመውታል፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ አንደኛው ፈተና የግድቡ ግንባታ ከሚከናወንበት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ የነበረው ሞቃታማ አየርና እሾሃማ ቁጥቋጦ ነው፡፡ እንዲሁም ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ ወንዙ ሙሉ አቅሙን አሰባስቦ የሚሄድበት በመሆኑ ከአንዱ ማዶ ወደ ሌላ ማዶ በዝናብ ወቅት ተሻግሮ ለመስራት ያስቸግር ስለነበር ተሻጋሪ ድልድይ በመገንባትና ያለውን የአየር ሁኔታ በመቋቋም ስራውን ማከናወን ተችሏል፡፡
ሌላው ያጋጠመው ፈተና ከግንባታው መጓተት ጋር ይያያዛል፡፡ በፕሮጀክቱ የብረታ ብረት ስራዎች (ጀነሬተር፣ ተርባይን፣ የውሃ ማስተላለፊያና መቆጣጠሪያ በሮች) የመስራት ኃላፊነት ተሰጥቶ የነበረው በወቅቱ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እየተባለ ይጠራ የነበረው (የአሁኑ ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ) ሲሆን፣ እስከ 2009 ዓ.ም ሁለት ተርባይኖች ሀይል እንዲያመነጩ ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ኩባንያው በአቅም ማነስ ምክንያት የገባውን ግዴታ መወጣት አልቻለም፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የግድቡ ግንባታ ስራ ሂደት ተገምግሞ ከኩባንያው ጋር የተገባው ውል እንዲቋረጥ እና አቅም ላላቸው የውጭ ሀገር ተቋራጮች እንዲሰጥ በማድረግ ግንባታው እንዲከናወን መደረጉን የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂኒዬር ክፍሌ ሆሮ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቁጥር 7 መጋቢት 2011 ዓ.ም በወጣው መፅሔት ላይ ከጻፉት ጹሁፍ መረዳት ይቻላል፡፡
ሌላውና ትልቁ ፈተና ከታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ከግብፅ ሲደረግ የነበረው ጫና ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት ስትጀምር፤ ከግብፅ በኩል “ተጀምሮ ይቆማል እንጂ አያልቅም” በሚል ለማጣጣል ይሞከር ነበር። የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነ ሲመጣ ለምሳሌ በ2005 ዓ.ም ግንባታውን ለማከናወን እንዲያመች የወንዙ የፍሰት አቅጣጫ እንዲቀየር ሲደረግ፤ “ውሃውን ለማቆም እየሰራች ነው” በሚል ክስ ማቅረብ ጀመረች፡፡ የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡም የተሳሳተ እይታ እንዲኖረው በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት አድርጋለች፡፡
በግንባታው ሂደት እንደታየው የግድቡ ግንባታ በየጊዜው እያደገ ሲሄድ የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ የሚያደርገው ድጋፍ በሁለንተናዊ መልኩ እየተጠናከረ እንደመጣ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ፍትሀዊ፣ ምክንያታዊና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ የውሃ አጠቃቀም መርህን በመከተል፣ በግድቡ ዙሪያ አስፈላጊ መረጃዎችን በመለዋወጥ፣ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲሳተፍ በማድረግ በሰራችው ስራ፤ ግብፅና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በ2007 ዓ.ም የመርሆች ስምምነትን ፈርመዋል፡፡ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ፍትሀዊ የተጠቃሚነት መብት እውቅና የሰጠ፣ በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ሶስቱም ሀገራት በትብብር እንዲሰሩ የሚያመላክት እንደሆነ የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ የግድቡ የውሃ ሙሊት ሊከናወን በተቃረበበት ወቅት ግብፅ እና ሱዳን “ከስምምነት ሳይደረስ ሙሊቱ መከናወን የለበትም” በሚል ተቃውሞና ክስ አቅርበዋል፡፡ በተለይ ግብጽ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የሌላቸው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1929 በግብፅ እና ታላቋ ብሪታኒያ እንዲሁም በ1959 በግብፅ እና ሱዳን መካከል የተፈረሙትን እና አጠቃላይ የወንዙን የውሃ መጠን ለሁለቱ ሀገራት ብቻ የሚሰጡት ስምምነቶች እንዳይነኩ በሶስትዮሽ ድርድሩ በብርቱ ሞግታለች፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም እንደሚገለፁት፣ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የግድቡ ግንባታ መጨመርና ግድቡ እውን ሊሆን ይችላል የሚል እምነት መያዝ ሲጀምሩ ያደርጉት የነበረው ጫና እየበረታ መጣ፡፡ በሚዲያ ጦርነት በመክፈት፣ በወታደራዊ ዘርፍ ግድቡን በአሻጥር ለመምታት፣ በዲፕሎማሲውም በአረብ ሊግ፣ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እና የተለያዩ ቀጣናዊና አህጉራዊ ተቋማት በመንቀሳቀስ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ሞክረዋል፡፡ በጎረቤትና የናይል ተፋሰስ ሀገራት በሆኑት እንደ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኤርትራና ጂቡቲ ባሉት ሀገራት ተዘዋውሮ በኢትዮጵያ ላይ ከበባ በማድረግ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባትም ሆነ የክረምት ወቅት ጠብቆ ውሃ መሙላቱን አላቆመችም፡፡ ግድቡ ውሃ ከያዘ በኋላ ለማፍረስ ቢያስቡም የሚያስከትለው መዘዝ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት የሀይል አማራጭን ትቶ በዲፕሎማሲው ጫና ማሳረፍ ላይ በማተኮር መስራታቸውን ረዳት ፕሮፌሰር አደም ያነሳሉ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ሰሞኑን በተላለፈውና “የኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ ከሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለይ ወደ መጨረሻ አካባቢ በሀገር ውስጥ ጦርነት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ዓለም አቀፋዊ ቀውሶችና ሌሎች መልከ ብዙ ፈተናዎች ባሉበት የተከናወነ ነው፡፡
“የግድቡ ግንባታ በጣም አድካሚና አታካች ስራ የነበረ ቢሆንም በፈጣሪ እርዳታ፣ በአቋምና አቅም ድማሮ፣ በህዝባችን ቁርጠኝነት፣ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታና በረሃውን ተቋቁመው ለዓመታት ሲሰሩ በቆዩ ጀግና ሰራተኞች የተከናወነ ነው፡፡ ህይወታቸውን ያጡ ሰራተኞች አሉ፡፡ ለግድቡ ግንባታ የሚሆኑ እቃዎችን ከጂቡቲ ወደብ ግድቡ እስከሚገነባበት ቦታ ድረስ የሚደርሰው ለወራት በሚፈጅ ጥበቃ ታጅቦ ነበር፡፡ በየቦታው ትናንሽ እሳቤ ያላቸው ሰዎች ሀገራዊ ጥቅምን ካለመገንዘብ፣ የላኳቸውን አካላት ፍላጎት ያሳኩ መስሏቸው ግንባታውን ለማደናቀፍ ብዙ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ ደምና ላብ ጠብ አድርገን፣ የውሃን ጠብታ ለቁም ነገር ያዋልንበት ስፍራ ነው፡፡” ሲሉ በግንባታው ሂደት ያጋጥሙ ስለነበሩ ፈተናዎች እና እንዴት ማለፍ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ጫና ማክሸፍ የቻለችው የፀና አቋም በመያዝ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት በመቻሏ ነው፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ በእስልምና ትልቅ ቦታ ያላቸው እንደነ ቢላልና ነጃሽ ያሉ ስብእናዎች፣ በነብዩ ሙሐመድ ትልቅ ክብር የተሰጣት በሙስሊሙ ዓለም የምትከበር ሀገር ናት። አፍሪካውያንም ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ላደረጉት ትግል ባበረከተችው አስተዋፅኦ ትልቅ ተሰሚነትና ክብር ያላት በመሆኑ በዲፕሎማሲው አሸናፊ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
“ኢትዮጵያ ጫናዎችን ተቋቁማ ግድቡን ለፍጻሜ ማብቃቷ የሚያኮራና የትውልዱ የአርበኝነት ተጋድሎ ተግባር ነው፡፡” የሚሉት የታሪክ መምህሩ ኑሩ ይማም በበኩላቸው፣ ያጋጠመውን ውስብስብ ፈተና ማሸነፍ የተቻለው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም፣ ከውጭ እርዳታና ብድር ይልቅ በራስ አቅም በመስራታቸው ነው፡፡ የዲፕሎማሲ ጫናውን ከግለሰብ ጀምሮ ዲፕሎማቶች፣ የሀገር መሪዎች፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ያሉ የሀገር ተወካዮች ባደረጉት ተጋድሎ ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል፡፡
“ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአሁኑ ትውልድ የአያት፣ ቅድመ አያቶች ጀግንነት፣ አልበገርምባይነትና ፅናት በልማት የደገመበት ታላቅ ስራ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ሌሎችን ሀገራት የመጉዳትና የማስፈራራት ፍላጎትም ሆነ ዓላማ የላትም” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም፣ ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ምክንያት በመላው ዓለም ላሉ ጥቁሮች የነፃነትና እኩልነት መብት መከበር ትልቅ መነቃቃት ፈጥራለች፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ፍትሀዊ እና በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ የውሃ አጠቃቀም መርህ በመከተል በትብብር መርህ እየሰራች እንደምትቀጥል የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ያስረዳሉ፡፡
የታሪክ መምህሩ ኑሩ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በውስጧ የተለያየ ቋንቋን፣ ሃይማኖትንና ባህልን ጨምሮ የተለያዩ ማንነቶች ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ ናት፡፡ ብዝሃነት ያላቸው ህዝቦች ቢሆኑም በሀገር ህልውናና ጉዳይ በአንድነት የመቆም ባህል አላቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ የመንግስት ስርዓታት ለህዝብ የማይመቹና ዴሞክራሲያዊ ባይሆኑም ማህበረሰቡ ግን ተሳስሮና ተጋምዶ በመኖር፣ የሀገር ሉዓላዊነትና ነፃነት ተጠብቆ ቀጥሏል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታም ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ የትውልዱን ዓድዋ መስራታቸውን አስረድተዋል፡፡
በጥቅሉ ኢትዮጵያ የመጣችበት መንገድ ጽኑ ህዝብ እንዳላት በግልጽ የሚያመላክት ነው፡፡ ይህንን ጽናት በቀጣይ ሊከወኑ በተወጠኑት ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ መድገምና ስሜቱንም ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ያስፈልጋል እንላለን፡፡
በስንታየሁ ምትኩ
#Ethiopia
#Dam
#GERD
#Development