“በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችጤናማ መሆን አለባቸው”

You are currently viewing “በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችጤናማ መሆን አለባቸው”

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር አየለ አዲስ (ዶ/ር)

• ሚድያው ማህበራዊ መስተጋብርን ከማጠናከር አንፃር አበርክቶው የላቀ እንደሆነም ተገልጿል

ዘመኑ የመረጃ ነው፡፡ መረጃዎች ከተለያየ አቅጣጫ በስልክ፣ በላፕቶፕ እንዲሁም በኮምፒዩተር አማካኝነት በብዛት ተሰራጭተው በሽርፍራፊ ሰከንዶች እጃችን ላይ ይደርሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከተቀረው የዓለም ክፍል ጋር በቅርበት እንድንወዳጅ ያደርገናል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ሠዎች የትኛውንም መረጃ ከማህበራዊ ሚድያ ያገኛሉ። ለጤናቸው የሚስማማቸውን መርጦ የመመገብ ጉዳይ ደግሞ የተጠቃሚው አካል ኃላፊነት ነው፡፡ ምክንያቱም ከእውነት የራቁ፣ አሉታዊ ዓላማን የያዙ፣ ለከፋ ተፅዕኖ የሚዳርጉ መረጃዎች ሲሰራጩ፤ በሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ሉዓላዊነት፣ በሕዝብ አንድነትና እሴት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ አደገኛ ነው፡፡

በዲጂታል ዘመን ስላለው መረጃ ስርጭት በመጠኑ ያነሳነው፤ “የጽናት ቀን” በሚል የተሰየመውን ጷጉሜን 1 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደ ሕዝብ ሀገረ መንግሥትን ለማጽናት የተከፈለውን መስዋዕትነት በማንሳት፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለው ትውልድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዴት ይወጣ? የሚለውን ጉዳይ ለመቃኘት ነው፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ በማህበራዊ ሚዲያ በርካታ ተከታዮች ያላቸውን የመረጃ አሰራጮች እና የዘርፉን ምሁር በማነጋገር ሃሳብና አስተያየታቸውን ይዘናል፡፡

“መረጃዎች ልክ እንደ ተቀጣጣይ እሳት ናቸው፡፡ በትክክለኛ ቦታ ላይ ትክክለኛ መረጃን ሳናስተላልፍ ስንቀር ወይም ስንዘገይ፤ የተሳሳቱ መረጃዎች አየሩን መቆጣጠራቸው አይቀሬ ነው” የሚለው በማህበራዊ ሚድያ ተፅእኖ ፈጣሪ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ቴዎድሮስ ተፈራ ነው፡፡ ይህ ወጣት በፌስቡክና በቲክቶክ ገፁ ላይ የተለያዩ ሀገርን ለማፅናት ብሎም ሉአላዊነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ መልዕክቶችን በመልቀቅ ይታወቃል፡፡ በቀን እስከ 10 የሚጠጉ የይዘት ስራዎችን በድህረ ገፁ ላይ የሚያሰፍር ሲሆን፤ በ28 ቀን ውስጥ መልዕክቶቹ እስከ 33 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች ይደርሳል፡፡ ከ165 ሺህ በላይ የሚሆኑ የፌስቡክ ተከታዮች አሉት፡፡

እንደ ወጣት ቴዎድሮስ ገለፃ፤ ማህበራዊ ሚዲያን ሀገርን ለማፅኛ እንደ አንድ መሳሪያ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ሀገራዊ ሰላምን ለማፅናት እና ለማጠናከር የሚያስችሉ ይዘቶች የትኩረቱ ማዕከል ናቸው፡፡ በተለይ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የጋራ ትርክት መሆኑን ተከትሎ በጋራ ስለመቆም የሚያወሱ ፅሁፎችን ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉም የተፋሰስ ሀገራት በዓባይ ወንዝ ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚ የመሆን መብታቸውን በተግባር ያሳየ ፕሮጀክት ስለመሆኑ፣ በሌሎች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ እንደሌለ፣ ይልቁንም ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ለተፋሰሱ ሀገራት መንግስታት፣ ሕዝቦች እና ለተቀረው ዓለም የማስረዳትን ኃላፊነት አቅሙ በፈቀደ መልኩ ሲሰራ ቆይቷል፤ በመስራት ላይም ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያውያን ኩራት ዓርማ እና መለያ ስለመሆኑ የሚያስገነዘብ ፅሑፍ፣ ምስል እና አጫጭር ቪዲዮዎች በማዘጋጀት በማህበራዊ ሚድያ ያጋራል፡፡ በጦር ሜዳ የሚከናወኑ ትግሎች የሀገርን መሰረት ለማፅናት በደምና በአጥንት  የተከፈሉ መስዋዕትነት ስለመሆናቸው ጭምር በቂ መረጃ ይሰጣል፡፡ እነዚህን ጨምሮ የማህበረሰቡን አሁናዊ ችግር የሚቀርፉ ብሎም በሀገር አንድነት ላይ መሰረት የሚጥሉ ይዘት ያላቸው ስራዎችን ለተከታዮቹ እና ለማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ያሰራጫል፡፡

በማህበራዊ ሚድያ የሚለቀቁ መረጃዎች አንድም እውነታን መሰረት ያደረጉ፤ አልያም ከእውነታው በእጅጉ የራቁ ሊሆን እንደሚችል የሚናገረው ወጣት ጌቱ መኮንን በበኩሉ፤  በዩቱብ፣ ቲክቶክ እና በፌስቡክ ለሀገር እና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን እያዘጋጀ ያሰራጫል፡፡ የሚያሰራጨው አንድ መረጃ 3 ሚሊዮን ሰዎች ጋር ተደራሽ እንደሚሆን የሚጠቁመው ይህ ወጣት፤ የሚያሰራጫቸው መረጃዎች እውነተኛነታቸው የተረጋገጠ መሆናቸው ላይ ትኩረት ያደርጋል። ከታማኝ ምንጮች የተገኙ፣ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ  መረጃዎች ለተከታዮቹ ማድረስ የእለት ተዕለት ተግባሩ ነው። የኢትዮጵያውያንን መፃኢ ተስፋ ሊያንፀባርቁ የሚችሉ መረጃዎችን ተደራሽ ያደርጋል፡፡ በተለይ ከሥራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ እንደ ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ ያሉ መርሃ ግብሮችን በማስተዋወቅ፤ ኢትዮጵያን ከአደጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ የራሱን ሙያዊ አበርክቶ እየተወጣ ይገኛል፡፡

በማህበራዊ ሚድያ አማካኝነት ሀገርን የሚያፀኑ፣ አንድነትን የሚሰብኩ እና አዎንታዊ ሚና ያላቸውን መረጃዎች ተደራሽ ለማድረግ ዓላማ ያደረገበትን ምክንያት ወጣት ጌቱ ሲያብራራ፤  “ባልተገባ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እንዲሁም በተሳሳተ የመረጃ ስርጭት በሀገርና በሕዝብ ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ፤ ʻእንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ እንዲህ አይፈጠርም ነበር’ በሚል የፀፀት ስሜት ላለመውደቅ እና ቀድሜ የምችለውን በማድረግ የዜግነት ግዴታዬን መወጣት ስላለብኝ ነው” ብሏል፡፡

“የሰዎች ማህበራዊ መስተጋብር መስመር መያዝ ሲችል ሀገር በሁለት እግሯ መቆም ትችላለች፡፡ ይህንን ለማሳካት ደግሞ በማህበራዊ ሚድያ ላይ ጥሩ ተሳትፎ ያለን ሰዎች እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለማህበረሰቡ የማስረዳት ኃላፊነት አለብን፡፡ ተከታዮቻችን የጠራ እውነት አግኝተው ለሌሎችም መረጃዎችን እንዲያጋሩ እናበረታታለን፡፡ በተለይ ጠቃሚነታቸው የገዘፉ መረጃዎች ሲኖሩም እንዲወዱት፣ አስተያየት እንዲሰጡ ብሎም ለሌሎች እንዲያጋሩ ጭምር የማነቃቃት ሥራ እንሠራለንም” ሲልም አክሏል፡፡

ያነጋገርናቸው በማህበራዊ ሚዲያ አዎንታዊ መረጃዎችን በማሰራጨት የሚታወቁት ወጣቶች፤ በቀጣይ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል፡፡ የተከታዮች ቁጥርን ከፍ በማድረግ ሀገርን በሚያፀና ብሎም ሉአላዊነቷን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ስራዎችን አጠንክሮ ለመስራት እቅድ አላቸው። ማህበራዊ ሚድያን ለበጎ ዓላማ ማዋላቸውን አጠናክረው በመቀጠልም የህሊና እርካታ ከማግኘት ባሻገር በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አሻራ ማስቀመጣቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር አየለ አዲስ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ ማህበራዊ ሚድያ አንድን ጉዳይ አንስቶ ሀሳቡን የህዝብ አጀንዳ ለማድረግ የሚያስችል የመረጃ መለዋወጫ ሁነኛ መሳሪያ ሆኗል፡፡ እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዩቱብ፣ ቲክቶክ፣ ቲውተር ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን በስፋት በመጠቀም መንግስታት፣ የተለያዩ ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የመገናኛ ብዙሃን እና ሌሎችም የራሳቸውን መረጃዎች ለዜጎች ያደርሳሉ። የእነዚህ መረጃዎች መሰራጨት የራሱ ዓላማ ይኖረዋል፡፡ ከተሠራጩ በኋላም አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

“ሀገረ መንግስትን ለማፅናት በማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚለቀቁ መረጃዎች ጤናማ እና ማህበረሰቡን የሚያክሙ መሆን አለባቸው” የሚሉት አየለ (ዶ/ር)፤ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀማችንን አዎንታዊ  እና አሉታዊ ውጤት ያለው በማለት በሁለት ይከፍሉታል።  እንደሳቸው ማብራሪያ፤ አዎንታዊ ውጤት ያለው የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም የመንግስት ተቋማት ስለ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የጤና ዘመቻዎች፣ የበጎ ፍቃድ ተግባራት፣ የመሰረተ ልማት ግስጋሴዎች፣ የሚጎበኙ የቱሪዝም ቦታዎች (መዳረሻዎች)፣ እየተሠሩ ያሉ ማህበረሰብ ተኮር ተግባራት የሚተዋወቁበት ነው፡፡

እንደ  አየለ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በማህበራዊ ሚድያ አማካኝነት ተሰጧቸውን ብሎም አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ይዘው ይወጣሉ፡፡ የግል ቢዝነሳቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ጠቃሚ እና አስተማሪ በሆነ መንገድ ያቀርባሉ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያን አሉታዊ ጎን በደንብ የምናስተውለው በፖለቲካዊ ግጭቶች ወቅት መሆኑን የጠቆሙት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህሩ፤ በሚድያው የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች፣ ሃሰተኛ እና የተዛቡ መረጃዎች በሀገር እና ሕዝብ ላይ አስከፊ ጉዳት ያስከትላሉ። ይህንንም በሀገራችን ተመልክተነዋል፤ እየተመለከትነውም እንገኛለን፡፡ አሉታዊ ተፅዕኖ በሚያሳድሩ መረጃዎች መሰራጨት ምክንያት የበርካታ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ ቤት ንብረታቸው  እንዲወድም ሆኗል ብለዋል፡፡

“ሀገርን ለማፅናት የግድ በጦር ሜዳ መሳተፍ አይጠበቅብንም፡፡ ይልቁኑም እጃችን ላይ በሚገኙ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ላፕቶፖች አማካኝነት ወደ ትግል ሜዳ በማቅናት ለሀገር ብሎም ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም፤ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ለማድረግ ማህበራዊ ሚዲያውን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በየአካባቢው የተሠሩ በጎ ተግባራትን በማህበራዊ ሚድያ አማካኝነት በድግግሞሽ ማህበረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ የፀናች ሀገርን መመስረት ይቻላል” የሚሉት አየለ (ዶ/ር)፤ የጋራ ትርክቶችን በማጠናከር ላይ የተመሰረተች ሀገር የትኛውም አካል ወደታች ቢጎትታት በቀላሉ የማትወድቅ፣ ቢጥላትም የማትሰበር እንድትሆን እንደሚያስችላት ጠቁመዋል፡፡

አየለ (ዶ/ር)፤ ማህበራዊ ሚድያን ሀገርን ለማፅት እንደ አንድ መሳሪያ መጠቀም ባልቻሉ ይልቁንም ባልተገባ ሁኔታ መረጃን ባሰራጩት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት እንደሚያደርስ የማይናማር እና የሲሪላንካ ሀገራትን ምሳሌ በማንሳት አስረድተዋል፡፡ እንደሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ በማይናማር በፌስ ቡክ ላይ የጥላቻ ንግግር በስፋት በመሰራጨቱ ምክንያት በጅምላ መፈናቀል፣ ቤት ንብረት መውደም፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስ ሆኗል፡፡ ʻአንድ ሀሰተኛ ሠው ያወራውን ሰባት ፈረሰኛ አይመልሰውም’ እንደሚባለው የሀሰተኛ መረጃዎች የስርጭት ፍጥነት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክረው ሌላኛው አባባል፤ ʻእውነት ጫማዋን እስከምታስር ድረስ ሀሰተኛ መረጃ ግማሽ ዓለምን ታዳርሳለች’ የሚባል ነው። ስሪላንካም በተመሳሳይ በማህበራዊ ሚድያ አማካኝነት የተሰራጨ ሃሰተኛ መረጃ ምክንያት የኢኮኖሚ ድቀትን አስተናግዳለች፡፡ ሀገራቱ ያስተናገዱት ጉዳት በገንዘብ አልያም በሌላ ነገር የሚተካ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገራት ልትወስደው የሚገባ በርካታ ትምህርት አለ ብለዋል፡፡ 

ማህበራዊ መስተጋብሮቻችንን ከማጠናከር አንፃር ማህበራዊ ሚድያ አበርክቶው እጅግ የላቀ ነው፡፡ ሰዎች እርስ በእርስ ክፍተቶቻቸውን እንዲሞሉ ብሎም እንዲረዳዱ ያደርጋል፡፡ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያን በተሻለ ለመረዳት በሀገርህን እወቅ ፕሮግራሞች  መረጃዎች በስፋት ይለቀቃሉ፡፡ ስለ አንድ ማህበረሰብ የአመጋገብ፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሚጎበኝ ቅርስ እና መሰል ትውፊቱ ምን እንደሚመስል ጭምር በማህበራዊ ሚድያ መረጃው ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል። ይህ እርስ በእርስ የመተዋወቅ ባህልን በማስፋት ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውጭ ሀገራት ከሚኖረው ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃ የሚለቅ እንዳለው ሁሉ፤ ለሀገር ግንባታ ብሎም ፀንቶ መቆም ምክንያት የሚሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በምትከውናቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ማስተዋወቅ ብሎም ለማህበረሰቡ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ዶክተር አየለ ሲያስረዱ፣ ሀገርን ለማፅናት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚከፈል መስዋዕትነት አለ፡፡ አንዱ ድል የማድረጊያ መሳሪያ ደግሞ ሚድያ በመሆኑ የሚለቀቁ መረጃዎች የጠራ እውነትን በማንገብ ማህበረሰቡ ዘንድ ተዓማኒነትን የማትረፍ ሚና መጫወት ያስችላሉ፡፡

ምሁራን እንዲሁ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ ብሎም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያበረክቷቸው ሙያዊ ትንታኔዎች ለሀገር እና ለሕዝብ ዕድገት ወሳኝ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የምሁራን በጥናት ላይ የተመሰረቱ ትንታኔዎች ለመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫን በማመላከት፣ ለማህበረሰቡ ንቃት ይጠቅማሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ትንታኔዎች በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መጠቀም ይገባል፡፡ ይህንን ዘመኑ የሰጠንን ጠቃሚ መሳሪያ በመጠቀም ሁሉም ዜጋ በተለይ የተማረው ማህበረሰብ አይተኬ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አየለ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወጣቶች እንዲሁ የበርካታ አቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት፣ በትራፊክ ማስተናበር፣ በደም ልገሳ እና መሰል የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ተሳትፈው በማህበራዊ ሚድያ በመልቀቅ ለበርካቶች ምሳሌ ለመሆን ችለዋል፡፡ በማህበራዊ ሚድያ አማካኝነት የሚለቀቁ መረጃዎች በጎ ተፅእኖ በማምጣት ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ በርካቶችንም በዚህ የተቀደሰ በጎ ተግባር ተሳታፊ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ ከዓመት ዓመትም የተሳታፊ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

በማህበራዊ ሚድያ ሀገርን ለማፅናት በሚሰሩ ስራዎች ከማን ምን ይጠበቃል? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ  አየለ (ዶ/ር)፣ “ማህበረሰቡ ‘ከሚለቀቁ መረጃዎች መካከል የትኞቹ ናቸው መልካም’ ብሎ ጥንቃቄ የተሞላበት የማረጋገጫ ስልት መጠቀም ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም የተሰሩ መልካም ስራዎችን የማስተዋወቅ ብሎም የማጋራት ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ ምሁራን ያላቸውን እውቀት በመጠቀም ሰፋ ያሉ ትንታኔዎችን ብሎም ሙያዊ ሃሳቦችን የማጋራት ኃላፊት አለባቸው፡፡ የሚድያ ተቋማት የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመመከት የሃቅ ማጣራትና ኃላፊነት የተሞላበት ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። መንግስትም የዲጂታል ትምህርትን በማጠናከር የሳይበር ወንጀልንና የጥላቻ ንግግር ላይ የንቃተ ህግ ትምህርቶችን በስፋት መስጠት ይኖርበታል” ሲሉ ሙያዊ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

#Socialmedia

#Hatespeech

#Society

#Information

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review