በአዲስ አበባ ባለፉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች መቅረባቸውን ይቀጥላሉ። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
የገጣሚና ደራሲ ዮሐንስ ሀብተማርያም ስራ የሆነው “ድርሳነ ጥላ” መጽሐፍ በሳለፍነው ረቡዕ ነሀሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም አራት ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጽሐፍት መደብር ተመርቆ ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱበት 16 አጫጭር ልብ ወለዶችን ይዟል፡፡ ዮሐንስ ሀብተማርያም ከዚህ ቀደም ለንባብ ካበቃቸው ስራዎች ውስጥ “አልፋ-ተረክ∫ ከሌሎች ደራሲያን ጋር በመተባበር፣ “ፍቅር ሰው ማኅሌት∫ን ደግሞ በግሉ የሰራቸው ይጠቀሳሉ፡፡
በሌላ መረጃ “የመያዣና የቀዳሚነት መብት ሕጎች በኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ አቶ ታደለ ቤዛ ሲሆኑ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ፣ አከራካሪ ጭብጦችን በማንሳት ጥሩ ትንታኔ የተደረገበት ነው ተብሏል። ፀሐፊው በባንክ ሕግ አገልግሎት ከ6 ዓመት በላይ ያገለገሉና በማገልገል ላይ ያሉ ሲሆን ይህን ልምድና ተሞክሮ ከባንክ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችን በጥሩ ሁኔታ ለመተንተን ተጠቅመውበታልም ተብሏል።
የኪነ ጥበብ ዝግጅት
“የሕብር ቀን ለሕብር ኢትዮጵያ ሕዳሴ” የተሰኘው መርሃ ግብር ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል፡፡ መርሃ ግብሩ የሚካሄደው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲሆን ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።
በተያያዘ ዜና ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ ጥበባት ውድድር በብሔራዊ ቴአትር ቤት ተካሂዷል፡፡ ተሰጥዖ ያላቸው ወጣቶችን መለየት፣ ማብቃትን እንዲሁም የኢትዮጵያን የጥበብ መሰረትን ማስፋት ዓላማ ያደረገው ይኸው ውድድር ከነሐሴ 28 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ውድድሩ “ሀገር እና ጥበብ፣ ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት∫ በሚል መሪ ሀሳብ የስዕል፣ የፋሽን ሾው፣ የድምፅና ውዝዋዜ እንዲሁም የመነባንብ ውድድርን ያካተተ ነበር። የሁሉም ክልሎች ቱባ ባህልና የኪነ ጥበባት ፀጋ ጎልቶ የወጣበት ውድድር እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡
የማስታወሻ መርሃ ግብር
“የምወድሽን እናስታውስ∫ በሚል አንጋፋዋ ጋዜጠኛና ደራሲ የምወድሽ በቀለን የሚዘክር መርሃ ግብር ትናንት ተካሄዷል፡፡ መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) የተካሄደ ሲሆን ታዋቂ ሰዎች፣ የምወድሽ ወዳጆችና አድናቂዎች ተገኝተዋል፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ ለአጭር ጊዜ ባጋጠማት ሕመም በሕክምና ስትረዳ ቆይታ ነሐሴ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ማረፏ ይታወሳል፡፡ በህይወት ዘመኗ በርካታ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃቸው የምወድሽ የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን አገልግላለች፡፡
የስዕል አውደርዕይ
“ወርቃማ ታሪኮች∫ የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ በዛሬ እለት ለእይታ ክፍት ይሆናል፡፡ ሰዓሊው እያሱ ሲሳይ ሲሆን አውደ ርዕዩ በፈንድቃ የባህል ማዕከል ከምሽቱ 11፡00 ሰዓት ይከፈታል፡፡ ይህ አውደ ርዕይ እስከ መስከረም 05 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል፡፡
እያሱ ሲሳይ የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ ሆኜ ያደረኩትን የ10 ዓመታት ጉዞ ለማስታወስ ይህን የጥበብ አውደ ርዕይ “ወርቃማ ታሪኮች∫ የሚል ርዕስ ሰጥቸዋለሁ፡፡ አውደ ርዕዩም በኢትዮጵያ ባህል፣ ወግ፣ አኗኗር፣ ውበትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር አስታውቋል፡፡
ቴአትር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በልዩ የአዲስ ዓመት መርሃ ግብር ምክንያት መደበኛ ቴአትሮች ካሳለፍነው ረቡዕ እስከ ነገ እሁድ ድረስ እንደማይታዩ አስታውቋል፡፡ መርሃ ግብሩ የማይኖረው “የሕብር ቀን ለሕብር ኢትዮጵያ ሕዳሴ” የተሰኘው ልዩ መሰናዶ ከነሃሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር እየተካሄደ በመሆኑ ነው፡፡
በቀጣይ ቀናት ግን በብሔራዊ ቴአትር ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ 11:30 ሰዓት ሸምጋይ፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ ቴአትሮች በብሔራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
በጊዜው አማረ