የነገ ሀገር ተረካቢው ትውልድ ብሩህ፣ ጤናማ፣ አምራች ዜጋና በሥነ ምግባር የታነፀ ሆኖ እንዲያድግ ከታች ከህፃናት ጀምሮ መስራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ከቅድመ ወሊድ እስከ ስድስት ዓመት ባለው የቀዳማይ ልጅነት ዘመን የሚደረግ እንክብካቤ በህፃናት ሕይወት ላይ መሠረት የሚጥል ነው። መልካም ጤንነት እንዲኖራቸው፣ በትምህርት፣ በስራ ዓለምና በህይወት ቆይታቸው ስኬትን እንሚያጎናጽፉ ራሱን የቻለ አወንታዊ ሚና እንደሚጫወት በዘርፉ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ይሁን እንጂ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአዲስ አበባ ለቀዳማይ ልጅነት ዘመን ትኩረት ሳይሰጥ በመቆየቱ የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. 2019 የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያካሄደው መለስተኛ የሥነ-ህዝብና ጤና ጥናት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሕፃናት ላይ ከፍተኛ ሲሆን በተለይም እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት መካከል 37 በመቶ የእድገት ውስንነት የመቀንጨር ችግር ይታይባቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ደግሞ 13 በመቶ የሚሆኑ እድሜያቸው እስከ አምስት ዓመት ያሉ ህፃናት መድረስ ከሚገባቸው የእድገት ደረጃ በታች እንደሆኑ ያሳያል፡፡
ታዲያ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን በመቅረፅ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ጤናና አምራች ትውልድ ለማፍራት እየሰራ ይገኛል። ወይዘሮ ህይወት ደረሰ በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ክትትል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አነሳሽነት የተመሰረተ ሲሆን እድሜያቸው ከዜሮ እስከ 6 ዓመት ያሉ ህፃናትን የሚያካትት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ ቢሮው ህፃናቱ በአካል፣ በአዕምሮና በሥነ ልቦና ጤናማ እንዲሆኑ ሦስት ተግባራት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው የህፃናትን የቀን ማቆያ ማዕከላትን ማስፋፋት ነው፡፡ ማቆያዎች ህፃናት ለአዕምሮ እድገታቸው፣ ለነገ ማንነታቸው ወሳኝ ነው የሚባለውን እድሜያቸውን ከሚያሳልፉባቸው፣ ሳይንሳዊ የሆነ እድገትን ሊያገኙ ከሚገባቸው፣ ደህንነታቸው ተጠብቆ ሊውሉባቸው ከሚገቡ ቦታዎች መካከል ናቸው፡፡
አራት አይነት የቀን የማቆያ አይነቶች አሉ፡፡ የመጀመሪው የስራ ቦታ የህፃናት የቀን ማቆያ ነው፡፡ በከተማዋ ባሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ለእናቶችና ለህፃናቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ ቢሮውም እነዚህ መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የማነሳሳትና ሙያዊ ድጋፍ የመስጠት እገዛ ያደርጋል፡፡
ሁለተኛው ማህበረሰብ አቀፍ የቀን ማቆያ ሲሆን፤ ይህም መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በተለይም እንደ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙባቸው ስፍራዎች ላይ ልጆችን ከጥቃት ለመከላከል፣ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ እንዲሁም ህፃን በመሆናቸው ከሚከሰቱባቸው ጉዳቶች ለመታደግ የተሰራ ነው፡፡
ሦስተኛው ሙሉ ወጭው በመንግስት የሚሸፈን ሲሆን፤ ከድህነት ወለል በታች ያሉ (ትንንሽ ስራዎችን እንደ ልብስ ማጠብ፣ እንጀራ መጋገር እና አሻሮ መቁላት የመሳሰሉትን ስራዎችን በልጆቻቸው ምክንያት መስራት ላልቻሉ) እናቶች ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህም ህፃናቱ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙበት፣ እድገታቸው በየጊዜው የሚረጋገጥበት፣ ደህንነታቸው የሚጠበቅበት፣ ለእናቶችም ደግሞ እረፍት አግኝተው የሚሰሩበትና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲጨምር እድል የሚፈጥር ነው፡፡
አራተኛው የእናቶች የቀን ማቆያ የሚባለው ነው፡፡ እናቶች በቤታቸው ባላቸው ቦታ ላይ ከራሳቸው ልጅ ውጭ ሌሎች ልጆችን ጨምረው ለራሳቸው ገቢ የሚያገኙበትና ማህበረሰቡንም ተጠቃሚ የሚያደርጉበት የማቆያ አይነት ነው፡፡
ቢሮው እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት ሁለተኛው ደግሞ ህፃናት በጨዋታ መማርን ወይም የህፃናት የመዝናኛና መጫወቻ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ነው፡፡ በውስጡም የሰንበት ዝግ መንገድ ወይም እሁድ እሁድ ለልጆች ደህንነታቸው የተረጋገጡ መንገዶችን በመዝጋት ከጠዋት እስከ 6፡00 ሰዓት ወጥተው እንዲጫወቱ የሚደረግበት እና በከተማዋ የተሰሩ የህፃናት መጫወቻ ቦታዎችን የሚይዝ ነው። እነዚህን መጫወቻ ቦታዎች ቢሮው ማህበረሰቡ ከማልማት ጀምሮ ቦታዎቹን እንዲጠብቃቸውና ልጆቹን እንዲያዝናና ግንዛቤ የሚፈጠርበት ነው፡፡
ሦስተኛው ተግባር የቀጥታ አልሚ ምግብ ድጋፍ ነው፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አማካኝነት እናት ከፅንስ ጀምሮ የተመጣጠነ ምግብ እንድታገኝ የማድረግ እና በሸማች ማህበራት በኩል ለነፍሰ ጡር፣ ለሚያጠቡና እድሜያቸው እስከ ሦስት ዓመት ላሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚደደረግበት መርሃ ግብር ነው።
የቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም መነሻው የልጆች እድገት በ14 በመቶ መድረስ ባለባቸው እድገት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ተረጋግጦ ይህንን ሊመልስ በሚችል መልኩ ወደ ስራ መገባቱን የነገሩን ዳይሬክተሯ፤ ትውልድ ላይ ካልተሰራ ነገ የተሻለ ዜጋ፣ የተሻለ ሀገር ተረካቢ ማፍራት አይቻልም ይላሉ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም ላይ አዲስ አበባ ልጅ ለማሳደግ ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ እንድትሆንና የትውልድ ግንባታ ላይ መሰረት አድርጎ እና ትልቅ አላማን ሰንቆ እየሰራ ነው፡፡ ይህም በዋናነት የተሻለ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ለህፃናቱ አስፈላጊውን እንክብካቤና ክትትል ማድረግ የአዕምሮና የአካል እድገት ላይ ሚናው ከፍ ያለ ነው፡፡
የቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ በቀጥታ አልሚ ምግብ ላይ ከ20 ሺህ 255 በላይ የሚሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በ11ዱም ክፍለ ከተማ በ119 ወረዳዎች ላይ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ተደርጓል፡፡ በዚህም በቀን ማቆያዎች አፋቸውን ያልፈቱ ህፃናት ቶሎ አፋቸውን እንዲፈቱ፣ እንቅስቃሴያቸው እንዲጨምር እና በዕለቱ የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ እንደተቻለ ነው ዳይሬክተሯ የነገሩን፡፡
“የነገዋ ኢትዮጵያ የዛሬ ህፃናት ውጤት ናት” የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ ብዙ በጀት
ወጥቶበት የተሰራ እና የነገውን ትውልድ የሚገነባ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወላጆችንም እፎይታ የሰጠ እና ከዚህ በፊት እድሜያቸውን የሚመጥን እንክብካቤ ሳያገኙ ለቆዩ ህፃናትም መፍትሄ እያስገኘ ያለ ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የእናቶች እና ህፃናት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንዱ መኩሪያ በበኩላቸው፤ የቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም ላይ ቢሮው በጤና ዘርፍ የሚመራውን የወላጆች የምክርና አቅም ግንባታ አገልግሎት እና በጤና ተቋማት የተቀናጀ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን በበላይነት እንደሚመራ ይናገራሉ፡፡
በዚህ መሰረት ቢሮው በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ክትትል ያደርጋል፡፡ በማህበረሰብ ደረጃ በሁሉም ወረዳዎች እና ብሎክ አደረጃጀቶች ላይ የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት የወላጆች የምክርና አቅም ግንባታ (ፓረንታል ኮቺንግ) አገልግሎትን በሰለጠኑ 5 ሺህ ሰራተኞች ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ፕሮግራሙን የመተግበር ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ጤና ቢሮው ጤና ጣቢያዎችን እና ሆስፒታሎችን ለህጻናት ምቹ እና ሳቢ እንዲሆኑ የማድረግ፣ ህጻናትን በጨዋታ የማስተማር ሥነ ዘዴን በመጠቀም ለወላጅ (አሳዳጊዎች) ትምህርት እና ስልጠና እንዲሁም ምክር መስጠት፣ ለህጻናት ሁለንተናዊ የዕድገት ክትትል ላይ መስራትና የመሳሰሉት ተግባራትን እንደሚያከናውን አብራርተዋል፡፡
ወይዘሮ ስንዱ እንደገለፁት፣ መርሃ ግብሩ ለህጻናት ጤና እና ዕድገት ወሳኝ እና ለወደፊት ህይወታቸው መሰረት የሚጣልበት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ህጻናት የተሟላ እድገት (በአካላዊ፣ አእምሯዊ፣ በቋንቋ ማለትም ተግባቦት እና በማህበራዊ ግንኙነት) እንዲኖራቸው በማስቻል ለወደፊት የተሟላ ጤና፣ ዕድገት፣ የትምህርት ውጤት እና አጠቃላይ በህይወታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ በማስቻል ለራሳቸው ብሎም ለሀገራቸው የሚጠቅሙ ትውልድ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ በተቀናጀ የጤና አገልግሎት (integrated approach) ስለሚሰጥ መደበኛ የጤና አገልግሎቱንም በማጠናከር የበኩሉን አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
የቀዳማይ ልጅነት ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ የህፃናት እድገት የጤና ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት ማዳበር ማስቻሉ፣ ጤና ተቋማት የህጻናት አገልግሎት መዳረሻ ክፍሎችን ለህጻናት ምቹ እና ሳቢ እንዲሆኑ መደረጉ እንዲሁም ህጻናትን በጨዋታ ማነቃቃት እና ለወላጅ ትምህርት መስጠት መቻሉ በህፃናቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ለውጦች እንዲመጡ አስችሏል፡፡ ቀድሞ የነበረው የማህበረሰብ ተሳትፎና ግንዛቤም በእጅጉ ጨምሯል፡፡
በቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም ላይ በጤና ተቋማት ከ800 ሺህ በላይ ለሆኑ ህጻናት በምልልስ የዕድገት ክትትል ተደርጓል፡፡ 237 ሺህ 83 አባወራ (ቤተሰብ) በፕሮግራሙ ቤት ለቤት ተደራሽ በማድረግ በልጅ አስተዳደግ እና በጨዋታ ማስተማር ላይ ስልጠና እና የምክር አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ 271 ሺህ 979 ከ6 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ቤት ለቤት በፕሮግራሙ ተደራሽ እንደተደረጉ እና ተከታታይ የሆነ ሁለንተናዊ የዕድገት ክትትል እንደተሰራላቸው የጤና ቢሮ የ2017 ዓ.ም መረጃ ያሳያል፡፡
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ትምህርት ክፍል መምህር አንተነህ አለም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ፣ የቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ በሥነ ምግባር ታንፆ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ከዚህ በፊት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ወይም አፀደ ህፃናት የሚያስተምሩና የሚንከባከቡ መምህራንን በማሰልጠን ሲሰራ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚሰሩ አካላት በጋራ በመሆን መሰራቱ ለትውልዱ ትኩረት መሰጠቱን አመላካች ነው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ፣ በጤናው ዘርፍ እና በትምህርት ቤቶች የሚሰራው ስራ በልጆች እድገት ላይ ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
የቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም የህፃናትን እድገት የሚያፋጥን፣ ጤናቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ፣ ልጆች በቀዳሚ የእድሜ ዘመናቸው የሚገባቸውን የእድገት ፍላጎት በማሟላት አእምሮአዊ፣ ማህበራዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ እድገታቸው የዳበረ እንዲሁም በመደበኛ ትምህርታቸውና በስራ አለም ብቁ ዜጋ የሚያደርግ ነው፡፡
አራት ዋና ዋና የህፃናት የእድገት ዘርፎች እንዳሉ የሚናገሩት መምህሩ፤ የመጀመሪያው በአካል ሲሆን ይህም ጥንካሬው፣ ክብደቱ ተመጣጣኝ መሆን፣ ሰውነቱን አንቀሳቅሶ የተለያዩ ነገሮችን ማከናወን መቻሉ የሚታይበት ነው፡፡ ሁለተኛው እድገት ማህበራዊና ስሜታዊ የእድገት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ የእድገት ዘርፍ የሚደረግላቸው እንክብካቤ፣ እገዛ፣ የሚሰጣቸው ትምህርት ለመኖር፣ የራስንና የሌሎችን ስሜት ለመረዳት የሚያስችልና ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው፡፡
ሦስተኛው የእድገት ዘርፍ የአዕምሮ እድገት ነው፡፡ በማሰብ፣ በማሰላሰል፣ በአካባቢ ያሉ ነገሮችን ተመሳሳይነትና ልዩነት በመገንዘብ እና በማስታወስ የሚያድጉበት ሲሆን የቀለም ትምህርት ይህንን ለማሳደግ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡
አራተኛው ደግሞ የቋንቋ እድገት ነው። ይህም የሚለካው ቋንቋውን መረዳት፣ መናገር፣ ማንበብና መፃፍ ሲችል እንደሆነ የሚናገሩት መምህር አንተነህ፤ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የጤና፣ የትምህርትና የመጫወቻ ቦታዎች ማስፋፋት ላይ ትኩረት ማድረጉ ፕሮግራሙ ህጻናት እድሜያቸውን የሚመጥን እንክብካቤ እንዲያገኙና ተገቢው እድገት እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ፣ መልካም ስብዕና ተላብሰው እንዲያድጉና ሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ መነሻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም እየሰራች ያለው ስራ ሁለንተናዊ ጤናው የተጠበቀ፣ አምራች፣ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር መሰረት የሚጥል፣ በቀላል ወጪ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እንላለን፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ