የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ከማዘመን ጀምሮ እስከ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ድረስ ያገኘነው ታላቅ ስኬት፤ የጋራ ዓላማችን እና ያላሰለሰ ጽናታችን ውጤት መሆኑን ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ገለጹ

You are currently viewing የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ከማዘመን ጀምሮ እስከ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ድረስ ያገኘነው ታላቅ ስኬት፤ የጋራ ዓላማችን እና ያላሰለሰ ጽናታችን ውጤት መሆኑን ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ገለጹ

AMN ጳጉሜን 1/2017

የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ከማዘመን ጀምሮ እስከ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ድረስ ያገኘነው ታላቅ ስኬት፤ የጋራ ዓላማችን እና ያላሰለሰ ጽናታችን ውጤት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ገለጹ።

“ጽኑ መሰረት፤ ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ ሐሳብ የጽናት ቀን እየተከበረ ይገኛል።

ዕለቱን አስመልክተው በአድዋ ድል መታሰቢያ በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም፤ ዛሬ የጽናት ቀንን ስናከብር ያለፉትን ድሎች ብቻ ሳይሆን፤ የወደፊቱን ተስፋዎቻችንን እየተቀበልን ነው ብለዋል። ጽናት የሚመራን ኮምፓስ፣ የአንድነታችን ኃይልና መንገዳችንን የሚያበራልን ነበልባልም ነው ብለዋል።

የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ከማዘመን ጀምሮ እስከ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ድረስ ያገኘነው ታላቅ ስኬት፤ የአንድነታችን፣ የጋራ ዓላማችን እና ያላሰለሰ ጽናታችን ውጤት መሆኑን በኩራት እናረጋግጣለን ሲሉም ገልጸዋል። ለእነዚህ ስኬቶች መንገድ የከፈቱት ጀግኖቻንን ድፍረት፣ የመስዋዕትነትና የማይናወጥ ጽናትን እናስታውሳለን፤ እናከብራለንም ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

የዛሬው ዕለት ፈተናዎችን ሁሉ ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይረን ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የብልጽግና፣ የክብርና የዘላቂ ከፍታ ለማድረስ ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል።

እንደ ኢትየጵያዊ የጀግኖቻችንን መንፈስ ተቀብለን ወደ ፊት ለመሻገር እንነሳ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ፈተናዎቻችንን ሁሉ ወደ መልካም አጋጣሚ እንቀይር፤ በተስፋ፣ በአንድነትና በዘላቂ ብልጽግና የተሞላ የወደፊት ዕድላችንን እንሥራ ሲሉም ተናግረዋል።

በአዲስ ተስፋ፤ በጽኑ መንፈስና በማይናወጥ አንድነት መቆም እንደሚገባ አስረድተው፤ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግናና ታላቅነት የምታደርገውን ጉዞ በይበልጥ ከፍ የምታደርግበት አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሀገራችን በጽናት፣ በጥንካሬ፣ በክብር እና በስኬት ትደምቃለች፤ የሚል የጋራ ርዕይ ይዘን በይበልጥ በቁርጠኝነት እንትጋ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review