ሃሳብ፣ ትጋት እና ጊዜ የወለዱት ፅናት

You are currently viewing ሃሳብ፣ ትጋት እና ጊዜ የወለዱት ፅናት
  • Post category:ፖለቲካ

AMN – ጳጉሜን 1/2017 ዓ.ም

የ13 ወር ፀጋ ባለቤት የሆነችው ሃገር ኢትዮጵያ፣ ይህንን የመታደስ እና የተስፋ መልእክትን ያነገበውን ልዪ ወሯን ጳጉሜን ብላ ትጠራዋለች።

በዚህ ዓመትም የዚህን ወር 5 ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች የምታከብር ሲሆን፣ የመጀመሪያውንም ቀን ፅናት ብላ ሰይማለች።

ፅናት ለኢትዮጵያ የመቆየት ጉዳይ ብቻ አይደለም.. የማስቀጠል፣ የክብር፣ የአላማም ጉዳይ እንጂ። ፅናት በፈተና ሰዓት ጠንክሮ መቆም ነው፤ ኢትዮጵያን ለክፍለ ዘመናት በፈተናዎች መሃል ተሸክሞ ያሻገራት ሃይል።

በማይንበረከኩ ተራራዎቿ፣ በድንጋይም መሃል ሰንጥቀው በሚያልፉ ወንዞቿ፣ ፈተናን ተቋቁመው ደግመው ደጋግመው በሚነሱ ህዝቦቿም ላይ የተፃፈ ነው።

ይህ ፅናት ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ አንፃር እንዴት ይታያል ስንል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ-ክርስቲያን ቀሲስ አዲስ ወ/መድህንን ጠየቅናቸው።

እውነተኛ ፅናት ሶስት ነገሮች ሲስማሙ ይወለዳል ነው ያሉት ቀሲስ አዲስ:፡ እነርሱም፡- ሃሳብ፣ ትጋት እና ጊዜ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

የማያወላዳ፣ የማይሸራረፍ፣ ተሻጋሪ፣ ገንዘብ ሊያደርጉት የሚችል፣ የሚታመኑለት አላማ ሲኖር:፡ ይህንንም አላማ ለማሳካት የማያባራ እና ያላሰለሰ ትጋት ወይም ጥረት ጊዜውን በጠበቀ፣ ጊዜውን በሚዋጅ፣ ጊዜውን በአግባቡ በተጠቀመ ድርጊት ሲታጀብ ውጤትን የሚያስገኝ ፅናት ይፈጠራል።

አንድ ተማሪ በሃሳቡ ሃገሩን፤ ወገኑን ስለመጥቀም ገዢ የሆነ ሃሳብ የሚያስብ ሲሆን፣ በትጋት እና በጥንካሬ ሲያጠና ፣ ጊዜውን በአግባቡ ሲጠቀም ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ፣ እነዚህ 3 ሃሳቦች ካልተስማሙለት ግን ውጤታማ መሆን እንደማይችል ልብ ይሏል፡፡

እነዚህ ሶስት ነገሮች የተስማሙለት ግለሰብም፣ ትዳርም፣ ተቋምም ይሁን ሃገር የፀና ነው ይላሉ ቀሲስ አዲስ፡፡ ኢትዮጵያ ፅኑ ናት፣ ህዝቡም ፅኑ ነው።

ሃገሪቱ የተመሰረተችው ተሻጋሪ በሆነ ሃሳብ ላይ ነው፣ መነሻዋንም መድረሻዋንም የምታውቅ ሃገር ናት፣ ህዝቡም ተሻጋሪ ነው።

ፅናት፣ ለሃገር መስዋእትነት በመክፈል የሚገኝ የክብር አርማ ነው።

ቀሲስ አዲስ ይቀጥላሉ፣ኢትዮጵያ የፅናቷ ተምሳሌት ከሆኑ ዋነኛው የአድዋ ድል ነው። በወቅቱ ህዝቡ ገንዘብ ሊያደርገው የሚችል የጋራ ገዢ ሃሳብ ነበረው፣ ሃገር የምትባል። ይህም ህዝብን በጋራ ያቆመ ሃሳብ ትጋትን በመውለድ በትክክለኛው ጊዜ ተከውኖ ድልን አቀዳጀ።

በጥንካሬ፣ በመስዋእትነት እና በማይናወጥ እምነት በአድዋ የተገኘውም ድል በአፍሪካና ከዛም አልፎ አስተጋባ። ታዲያ የአድዋ ድል በአንድ ቀን የተገኘ ድል አይደለም: ከራዕይ፣ ከቁርጠኝነት እና ከጊዜ የተወለደ የፅናት ፍሬ ነው።

ዛሬም የኢትዮጵያ ፅናት በህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ላይ ደምቆ ታይቷል። ገንዘብ ሊያደርጉት በሚችሉት፣ ተሻጋሪ በሆነ ሃሳብ የተጀመረው የህዳሴ ግድብ፣ በብዙ ውጣውረዶች መሃልም ቢሆን ባላሰለሰ ትጋት፣ በጊዜው እና ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ ተጠናቋል። ኢትዮጵያ አትችይም የተባለችውን ችላ አሳይታለች፣ ጠላቶቿን አሳፍራለች።

ኢትዮጵያ ለአመታት በፈተና ውስጥ ብታልፍም፣ የውስጥ እና ውጪ ጫናዎች ቢደራረቡባትም፣ የጋራ ክንዷን አበርትታ ግድብን ብቻ ሳይሆን የፅናት ምልክትን፣ የመጪው ትውልድ ተስፋን ገንብታለች።

የህዳሴ ግድብ ለጋራ አላማ አንድ ላይ ለቆሙ፣ ለአላማቸው ለተጉ እና ጊዜያቸውን ለተጠቀሙ ህዝቦች የትኛውም ፈተና ታላቅ እንደማይሆን ማሳያ ሆኗል።

ከለዉጡ ወዲህ በሃገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ድሎችም የጽናት ተምሳሌቶች ናቸዉ፡፡

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review