የጽናት ቀን “ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ በሀረር ከተማ ኢማም አህመድ እስታድየም በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በፅናትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ማንሰራራት ከዳር ለማድረስ በጋራ መትጋት አለብን ብለዋል።
ለዘላቂ ልማትና ለእድገት በፅናት በመትጋት ለትውልዱ የምትመች ሀገር በጋራ የመገንባት ተግባራን ይበልጥ አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከምንግዜውም በላይ የፅናት ማሳያ ስራዎች የተመዘገቡበት መሆኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ በሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ በእንድነትና ቁርጠኝነት የተገነባው የህዳሴ ግድብ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተውፊቅ መሀመድ፤ በኢትዮጵያዊያን ትብብርና ጽናት ሰላምን በማጽናትና በማስቀጠል የልማት ግቦቻችንን ማሳካት አለብን ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ኢዜአ ያነጋገራቸው የፀጥታ ሃይሎች ጀግኖች ያስረከቡንን ሀገር በፅናትና ጀግንነት ክብሯንና ሉዓላዊነቷን የመጠበቅ ሃላፊነታችንን መወጣታ ይቀጥላል ብለዋል።
በአከባበሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመከላከያ እና የፖሊስ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።