የጋራ ምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባትና ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጎልበት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው

You are currently viewing የጋራ ምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባትና ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጎልበት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው
  • Post category:ፖለቲካ

AMN ጳጉሜን 1/2017

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባትና ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጎልበት የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው የ2017 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ፣ የ2018 ዕቅድ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምርቃት ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ጉባኤው መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ጠንካራ፣ ዘላቂ ልማት፣ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት እና ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለህዝቦች አብሮነት፣ መቻቻል እንዲሁም ለሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ጉልህ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ የጋራ ድምጽ የሚሰማበት መድረኮችን በመፍጠር ብሎም በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚዊ እና ማህበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን በርካታ ስራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል፡፡

መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት ከማድረግ አኳያም በጋራ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎች ይበልጥ አሳታፊ፣ አካታችና ነጻ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን በጋራ የመፍጠር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ያላቸውን የፖለቲካ ፍላጎት እውን ከማድረግ ጎን ለጎን ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር የመሥራት መልካም ጅማሮዎች መኖራቸውን ማንሳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

ለአብነትም 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review