ለቡና ምርትና ምርታማነት ማደግ የተሰጠው ትኩረት የላቀ ውጤት እያመጣ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ በመገኘት በቀርጫንሼ ግሩፕ የለማውን የቡና ልማት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት ማብራሪያም ለቡና ልማት በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለቡና ምርትና ምርታማነት ማደግ የተሰጠው ትኩረት የላቀ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸው፤ በቀርጫንሼ ግሩፕ በገላና ወረዳ በ750 ሄክታር መሬት ላይ የለማው ቡና ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።
የቡና ልማቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ለቡና ጥራትና ምርታማነትም ጥሩ ተሞክሮ የታየበት መሆኑን ገልጸው፤ መሰል የልማት ስራዎችን የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ የቀጥላል ብለዋል።
የቡናን ልማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ ጥራትንና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል በቀርጫንሼ ግሩፕ የቡና ልማት ማረጋገጥ ችለናል ነው ያሉት።
የቀርጨንሼ ግሩፕ ሥራ አስኬያጅ እስራኤል ደገፋ (ዶ/ር) ለልማቱ በመንግስት እየተደረገ ያለው እገዛና ድጋፍ ለውጤታማነት ያበቃቸው መሆኑን አንስተው በቡና ጥራትና ምርታማነት ስኬታማ ሆነናል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ቡናን ከጥላ ዛፍ ውጭ ማልማት በገላና ወረዳ ከ750 ሄክታር በላይ መሬት ላይ መከናወኑን ገልጸው የላቀ ውጤት እየተገኘበት ስለመሆኑም ተናግረዋል።