ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማፅናት በጀመርነው ተግባራዊ ሥራ ሀገራዊ ተቋማት ከፍተኛ ሚና አላቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ በፅናት ቀን በሚድሮክ ኢንቨስትመነት ግሩፕ የተዘጋጀውን ዐውደ ርዕይ ተመልክተናል ብለዋል፡፡
በደም እና በአጥንት የፀናች ሀገርን በኢኮኖሚ ልዕልናዋ እንዲረጋገጥ የግሉ ዘርፍ በልማቱ የሚያበርክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ድርሻ ይይዛል ሲሉም ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ በተለያዩ ፈታኝ ወቅቶች ጭምር በፅናት በመስራት ሕዝባዊነታቸውን ካረጋገጡና ለሀገር ኢኮኖሚ እንዲሁም ማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ ተቋማት ውስጥ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አንዱ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
ተቋሙ ባሉት 45 ኩባንያዎች ለሀገር እና ሕዝብ ከሚያበረክተው ቀጥተኛ ድጋፍ ባለፈ ምርቶቹን በቅናሽ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረቡን አንስተዋል።
በተጨማሪም ሌሎች ተቋማት የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው በር መክፈቱና የካበተ ልምዱን ለማሳወቅ ይህንን ዐውደ ርዕይ ማዘጋጀቱ በአርአያነት የሚቀርብ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ የሀገር ዕድገት እና ብልፅግና ከግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ውጪ የሚታሰብ እንዳልሆነም አመላክተዋል።
ለዚህ ደግሞ እንደ ሚድሮክ ሁሉ ዓመታትን የተሻገር ልምድ ያላቸው ተቋማት ልምዶቻቸውን ማጋራት እና ህዝባዊነታቸውን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ ለማፅናት ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል።