ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀዉ 2ኛዉ የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

You are currently viewing ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀዉ 2ኛዉ የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
  • Post category:አፍሪካ

AMN ጳጉሜን 2/2017

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ብቻ ሳትሆን መፍትሔዎችን በማመንጨት የተግባር ምላሽ እየሰጠች የምትገኝ አህጉር ናት ሲሉ የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።

በጉባኤው ላይ ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎም ይጠበቃል። ተፈጥሮ ተኮር የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችን ማስፋት ከጉባኤው አጀንዳዎች መካከል አንዱ መሆኑም ይታወቃል።

የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በጋራ በሚመክርበት ወቅት አፍሪካ ለቀውሱ የተቀናጀ ምላሽ መስጠት ላይ ክፍተት እንደነበረባት ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ አህጉሪቷ ድምጿ እንዲሰማና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደማጭነት ለመጨመር እንደሚያዝ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት አስተዳደር ያላት የፖለቲካ ፍላጎት እና አመራር ሰጪነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር አጀንዳዎችን በመቅረጽና ቃል ኪዳኖች ወደ ሚጨበጡ ስራዎች በመቀየር ስኬታማ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እና በፈቃደኛነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ እቅድ ምላሽ ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት ፖሊሲዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በእቅዱ መሰረት ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2030 የበካይ ጋዝ ልቀትን በ68 በመቶ የመቀነስ እቅድ ይዛለች። ሁሉን አቀፍ ፖለሲዎቹ ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ያላትን ቁርጠኝነት እና ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ተግባር እያከናወነች እንደሚገኝ ማሳያ መሆኑን ነው ሰብሳቢው የገለጹት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተጀመረው አረንጓዴ አሻራ እስከ አሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

አረንጓዴ አሻራ የአፍሪካ ተፈጥሮ ተኮር የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ማሳያ ነው ያሉት ሰብሳቢው መርሃ-ግብሩ የደን ሽፋን መጨመር እና ብዝሃ ህይወትን መጠበቅን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን መፍትሄዎችንም የማቅረብ አቅም ያላት አህጉር እንደሆነችም ነው የገለጹት።

እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ኢኒሼቲቮችን በታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ ስር በማስፋት አህጉራዊ ምላሽን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የገባቸውን ቃል ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበት ማሳሰባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል። የአፍሪካ መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ መፍትሄዎችን መተግበር ላይ አበክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review