ኢትዮጵየ የኅብር ውጤት ናት

You are currently viewing ኢትዮጵየ የኅብር ውጤት ናት

AMN-ጳጉሜ 02/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የጥካሬ ምንጭ ከኢትዮጵያውያን ኅብር ይቀዳል። የህዝቦቿ ዘመን አይሽሬው አንድነት የወል ውበት ለሆነው ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ባህር ተሻግሮ ሀገር ለመበዝበዝ የመጣን ጠላት ዕድሜ፣ ፆታ ፣ ብሔር ሀይማኖትና ውስጣዊ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ዛሬም ድረስ ዓለም በአግራሞት የሚያስታውሰውን የአድዋ ድል የተቀዳጀች ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ።

“ብዝሀነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ኢትዮጵያ የኅብር ውጤት የሆነች ሀገር ናት ብለዋል።

ኅብር ስጠናከር ሠላም ይጎላል ያሉት ሚኒስትሩ የዘመናችን አድዋ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብም የኅብር ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጳጉሜ ወር የተስፋ፣የይቅርታ እና ለአዲስ ሥራ የምንዘጋጅበት ወቅት ሲሆን የወል ትርክት፣ ሀገራዊ መግባባት እና ኅብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ዓላማ በማድረግ በተለያዩ ስያሜዎች እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን በማዳከም ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማሳካት የሚሹት ሀይሎች የነጠላ ትርክቶችን መፈብረክ ላይ የተጠመዱ ቢሆንም በደም እና አጥንት የተሰናሰለው ኢትዮጵያዊነት ለመሰል እሳቤዎች ቦታ የማይሰጥ ነው ብለዋል፡፡

መንግስት የወል ትርክት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን በኅብር ያሳካናቸው አስደሳች ትሩፋቶች አሉ፤ በቀጣይም በኅብር ብዙ የምናስመዝግባቸው ድሎች አሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሃና አርአያስላሴ በበኩላቸው ኅብር በብዝሀነት ውስጥ የተሰናሰለ አንድነት ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በብዝሀነት የደመቀች ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ለሀገራዊ እሴቶች ትልቅ ቦታን የሰጠች በመሆኑ ኅብረብሔራዊ አንድነታችን ይበልጡን የጠነከረበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

በኅብር ያሳካነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አንዱ የኅብር ስኬት ነው ያሉ ሲሆን ይህም አጋጥመውን ለነበሩ ፈተናዎች በቀላሉ መፍትሔ ለማበጀት እና ለመሻገር ያስቻለ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

እጅ ለእጅ ተያይዘን ድል ያደረግነው በሕብረታችን በመሆኑ በቀጣይም የኅብር ጉዞአችንን አጠናክረን ብዙ ሀገራዊ ድሎችን በመጎናጸፍ ወደ ጀመርነው ሀገራዊ ከፍታ እንወጣለን ብለዋል፡፡

በመድረኩ የጋራ ታሪክ፣ ባህል እና ብዝሀ ማንነት፤ ማህበራዊ ባህላዊ እሴቶች እና ኅብረብሔራዊ አንድነት በኢትዮጵያ እንዲሁም የሚዲያ ሚና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ በሚል ለፓናል ውይይቱ የሚሆን የመነሻ ፅሑፍ በተለያዩ ምሁራን እና ተመራማሪዎች የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎችም በፅሁፉ ላይ ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ፣የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያስላሴ፣የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ኘሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፣ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ተመራማሪዎች እንዲሁም ሌሎችም የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

#Ethiopia

#Unity

#Addismedianetework

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review