ጳጉሜ-2 የህብር ቀን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደመቀ ስርዓት ተከበረ

You are currently viewing ጳጉሜ-2 የህብር ቀን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደመቀ ስርዓት ተከበረ

AMN – ጳጉሜን 2/2017 ዓ.ም

ጳጉሜ-2 የህብር ቀን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋናው መ/ቤትና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች በተገኙበት ህብር፣ አንድነት፣ የጋራ ታሪካችንና እሴቶቻችንን በሚያንፀባርቁ የተለያዩ ኩነቶች በደመቀ ስርዓት መከበሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳም ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር፤ የዘንድሮው የህብር ቀን ሀገራችን ታላቁን የህዳሴ ግድብ አጠናቃ ለማስመረቅ በተዘጋጀችበት ዋዜማ ላይ መገኘታችን የህብር ቀንን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

አቶ አዳም ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሀገራችን ህብረብሄራዊነታችን የታየበት የዳግም የዓድዋ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

በ2017 ዓ.ም. ሀገራችን በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ውጤቶችን ያስመዘገበችበት ዓመት መሆኑን አብራርተዋል።

በዝግጅቱ “ብዘሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በፓናል ውይይቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባባሪያ ጽ/ ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ( ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ፕ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) የተሳተፉ ሲሆን አምባሳደር ፍጹም አረጋ በአወያይነት መርተዋል።

በፓናል ውይይቱ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ያልሙት የነበረውን፤ ያደርጉታል ተብሎ የማይታሰበውን የዓባይ ውሃን ገድበው ለሀገር ጥቅም ማዋል የቻሉበት ወቅት ላይ እንደሚገኙ ይህም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭት የወለደው ውጤት መሆኑ ተገልጿል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሀገራችን የተለያዩ ተግዳሮቶችን መጋፈጧ፤ በተለይ በዲፕሎማሲው መስክ እልህ አስጨራሽ እንደነበር በመጨረሻም ህዳሴ ግድብ የዲፕሎማሲያችን ውጤት የአብሮነታችን ስኬት በመሆን ለውጤት መብቃቱ በውይይቱ ተገልጿል።

በዕለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት አመታት ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እና መ/ቤቱ ለሚያሳድጋቸው 33 ህጻናት የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የጉለሌ ህጻናት ማዕከል ታዳጊዎች ዕለቱን በማስመልከት ዓባይ በሚል ዜማዎችን ማቅረባችን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review