አፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት በመደመር እሳቤ ለጋራ ብልፅግና በጋራ መቆም እንዳለባቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing አፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት በመደመር እሳቤ ለጋራ ብልፅግና በጋራ መቆም እንዳለባቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN ጳጉሜን 2/2017

አፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት በመደመር እሳቤ ለጋራ ብልፅግና በጋራ መቆም እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሁለተኛው የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ የመሪዎች ስብሰባ በአፍሪካ ሕብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት አሸናፊነት በሀይል ወይም በጀግንነት ሳይሆን በአንድነት በመቆም ነው።

የአፍሪካና ካሪቢያ ሀገራት ችግሮቻቸውን መፍታት የሚችሉት በመለያየት አይደለም፣ አንድ በመሆን እንጂ ብለዋል። አፍሪካ ከካረቢያን ሀገራት ማህበረሰብ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማጠናከር እንዳለባትም ገልጸዋል።

የመደመር እሳቤ የአላማ አንድነት መፍጠር መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እየተቀየረ በመሆኑ በአንድ ድምፅ መናገር አለብን ብለዋል። ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ቀጣናዊ ትብብርን እንደሚፈልጉ በመግለጽ፤ እንደ እኛ ያሉ ደግሞ ግልጽ ትብብር እንጂ በተናጠል መንቀሳቀስ አይገባቸውም ብለዋል።

አፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት ማህበረሰብ ያላቸውን አቅም በማስተባበር አንድነታቸውን በተለያዩ መንገዶች ማጠናከር አለባቸው ብለዋል። ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ከትብብርም በላይ የጋራ ጥረትና የአላማ አንድነትን በማጎልበት ሀሳብ ወደ ተግባር፣ ወደ ዘላቂ ለውጥ እየቀየረች መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ትልቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በማስተሳሰር ቀዳሚ የትራንስፖርት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ የህዝብ ለህዝብ፣ የሀሳብና የኢኮኖሚ ትብብር ፈጥሯል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ስርዓተ ምህዳሩን መመለስና የስራ ዕድል መፍጠር መቻሏን ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገው የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ከውጭ ከማስገባት ወደ ዓለም ገበያ የማቅረብ ሂደት ተሸጋግሯል ብለዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ ለንግድና ፋይናንስ አዲስ መንገድ መክፈቱን ገልጸው፣ሀገር በቀል መፍትሔዎች ኢኮኖሚውን በማሳደግ ራሳችንን አስችሎናል ነው ያሉት። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ፋይናንስ ጉልበትና መስዋዕትነት የተገነባ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስንተባበር ጠንካራ እንደምንሆን አሳይቷል ብለዋል።

እነዚህ ስኬቶች የመደመር ውጤቶች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከካሪቢያን ሀገራት ማህበረሰብ ጋር ለጋራ ብልፅግና መተባበር አለብን ማለታዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ግብርና፣ ኢነርጂ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ እውቀት ለአፍሪካና የካሪቢያን ሃገራት ማህበረሰብ የብልፅግና ድልድይ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review