አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በይዘት ጥራትና አቀራረብ ከከተማዋ አልፎ በሃገር አቀፍና በአህጉር ደረጃ ተመራጭና ተወዳዳሪ ሚዲያ ለመሆን በትጋት እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሣሁን ጐንፋ ገለጹ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ 24/7 ማስጀመሪያና የአዲስ ስቱደዮ ምረቃ መርሃ ግብር አካሄዷል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ የኤኤምኤን የቦርድ አባል ብርሃኑ ሌንጅሶ(ዶ/ር) እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሣሁን ጐንፋ አዲሱን ስቱደዮ በመመረቅ 24/7 ን አስጀምረዋል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሣሁን ጐንፋ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ተቋሙ በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ በመሆን ወቅታዊ መረጃዎችን በተለያየ ቋንቋዎች ተደራሽ በማድረግ የህዝብ ድምፅነቱን እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተወዳዳሪና ተመራጭ ሚዲያ ለመሆን በይዘትና አቀራረብ በኩል ካደረገዉ ዝግጅት በተጨማሪ ዘመናዊ የሚዲያ ቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ 24/7 በመሥራት የስራ ባህልን በመቀየር የሚታይ ለውጥ ማምጣቷን የተናሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከተማዋን የሚመጥን እና ከለዉጡ ጋራ የሚራመድ ሚዲያ ለመሆን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከከተማዋ አልፎ በሃገር አቀፍና በአህጉር ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሚዲያ ለመሆን የያዘዉን ራእይ ለማሳካት በአዲሱ አመት 2018 ዓ.ም አዲስ ይዘት፣ አዲስ አቀራረብና የተሻለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም መረጃዎችን በፍጥነትና በተአማኒነት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም ከአዲሱ ስቱዲዮ በተጨማሪ አዳዲስ ይዘቶችን በማዘጋጀት በአዲሱ አመትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ዋዜማ ወደ ስራ መግባቱን አብስረዋል፡፡
ተቋሙ በቀጣይ የህዝብ ድምፅ በመሆን ተወዳዳሪና ተመራጭ ሚዲያ ለመሆን ሁሌምይተጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀዉ የበጀት አመት ለተቋሙ የሰጠዉ እዉቅናና ሽልማት የተሻለ እንድንሰራና ህዝባችንን በታማኝነት እንድናገለግል ትልቅ አቅም ፈጥሮልናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ 24/7 ማስጀመሪያና የስቱደዮ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ የተቋሙ የማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ አመራሮች ፤ ሰራተኞችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በበረከት ጌታቸዉ