አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በለውጥ ጉዞ ላይ እንደሚገኝ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለፁ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ባለፉት ዓመታት በከተማዋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መረጃን በፍጥነትና በጥራት ወደ ህዝቡ ሲያደርስ ቆይቷል።
የትውልድ ድምፅ የሆነው ተቋሙ ይበልጥ ተወዳዳሪና ተመራጭ የሚያደርገውን አዲስ አሰራር በመዘርጋት ኤ ኤም ኤን 24/7 ማስጀመሪያና የአዲሱ ስቱዲዮ ማስመረቂያ ስነ ስርዓት አካሂዷል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ የኤኤምኤን የቦርድ አባል ብርሃኑ ሌንጅሶ(ዶ/ር) እና የኤ ኤም ኤን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋን ጨምሮ የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ ድል ብስራት የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን አጠናቀን በምናስመርቅበት ዋዜማ ላይ ተቋሙ ሪፎርም በማድረግ መረጃን ከምንጩ ለህዝቡ ለማድረስ የሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን በምረቃ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኤ ኤም ኤን ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናግረዋል።
ተቋሙ የትውልድ ድምፅ በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠንካራ ስራን በመስራት በአስደናቂ የለውጥ ጉዞ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፤
የመጪው ትውልድ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በአቅም ግንባታና በይዘት ስራው መረጃን ከምንጩ በጥራት እና በፍጥነት በማድረስ ተመራጭና ተደማጭ ሚዲያ እንደመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አብራርተዋል።
አዳዲሰ ይዘቶችና ቴክሎጂዎችን በመጠቀም ኤ ኤም ኤን 24/7 በሚል አቀራረብ መምጣቱ በከተማዋ የተጀመረዉን የስራ ባህል ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።
ከተማዋ ሌት ተቀን እየተገነባች ለሌሎችም ምሳሌ እንድትሆን ለአድማጭ ተመልካቹ ይህን ታሳቢ አድርጎ መስራቱ የሚያስመሰግን በመሆኑ ህብረተሰቡም በባለቤትነት ሊሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኤኤምኤን ያቀደዉን ዉጥን እንዲያሳካ የከተማ አስተዳደሩ ተገቢዉን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አክለዋል።
በሚካኤል ህሩይ