በጥናት ላይ በተመሠረተ ኦፕሬሽን በርካታ የተሽከርካሪ ዕቃዎችን በቁጥጥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ጎላ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተሠረቁ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን በመግዛት መልሠው የሚሸጡ ግለሠቦች ላይ ፖሊስ የወንጀለኞች ጥናት ሲያከናውን ቆይቷል።
ፖሊስ በጥናት የተለዩ ግለሠቦች ላይም ተገቢውን የፍርድ ቤት የመያዣና የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት፤ በአንድ ሸራ ቤት ላይ ባከናወነው ብርበራ ከተለያዩ አካባቢዎች ተሠርቆ የተከማቸ 175 የኋላ ፍሬቻ፣ 236 የፊት መብራት፣ 593 ጌጣ ጌጥ፣ 144 የተሽከርካሪ አርማ፣ 74 ጎማ፣ 94 ስፖኪዮ፣ 47 ዘመናዊ የመኪና ውሃ መርጫ እንዲሁም ልዩ ልዩ የተሽከርካሪ እቃዎች በቁጥጥር ከአንድ ተጠርጣሪ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

የተሽከርካሪ እቃ ጠፋብኝ የሚል ማንኛውም ግለሰብ በልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጎማ ቁጠባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በአካል በመቅረብ ንብረቱን መለየትና መረከብ እንደሚችልም ተገልጿል።
ህብረተሰቡ በተለያዩ አካባቢዎች ተሽከርካሪውን አቁሞ ዕቃ በሚሠረቅበት ወቅት የራሱን ንብረት በድርድር መልሶ ከመግዛት ይልቅ፤ በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ በማመልከት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስቧል።