ዓመቱ ያልተሞከሩ እና ያልተደፈሩ ጉዳዮች ፈጠራ በታከለበት ፍጥነት ተከውነው ኢትዮጵያን ተስፋ የሚጣልባት የዕምርታ ምድር አድርጓታል።
በታሪኳም ወርቅና ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የተባለለትን የውጭ ምንዛሬ ያገኘችበት ነበር፣ 2017 ዓ.ም። ለወትሮው ስንዴን በእርዳታ መልክ ታስገባ የነበረች ሀገር ለውጡን ተከትሎ በታየው የስንዴ አብዮት እና በተከታታይ የተመዘገበው ዕምርታዊ ውጤት አሁን ላይ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር መሆኗ የተለገፀበትም ዓመት ነው።
በማር፣ በወተት እና በዶሮ ምርት ላይ ያተኮረው የሌማት ትሩፋት መርሀግብርም በጉልህ ከሚነሱ ዕምርታዎች መካከል ተጠቃሽ ነው ። የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ፣የምገባ፣ የበጎፈደቃድ አገልግሎትች እና ሌሎችም ሰው ተኮር ሥራዎች በዓመቱ ትልቅ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ጉዳዮች መሆናቸውን ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከኒውዮርክ እና ጄኔቭ ቀጥሎ ዓለም ዓቀፍ ኮንፍረሶንችን በማስተናገድ ቀዳሚ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ዝናዋና መልኳ የተጣጣመበት ዓመት መሆኑን ነዋሪዎች ይገልፃሉ። ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ባልተለመደ ፍጥነትና ጥራት መከናወኑ ደግሞ ለነዋሪዎቸ ደስታን የፈጠረ ሌላኛው ዕምርታ ነው።
ዕምርታው በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመንን የሚያጎለብት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል ። በስስትም በጉጉትም የሚጠብቁት እና የኢትዮጵያውያን አሻራ የታተመበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በቃላት የማይገለፅ ልዩ ስሜትን ፈጥሮላቸዋል።
በኢንዱስትሪው፣ በግብርናው ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጥራ እና በልዩ ልዩ መስኮች የተመዘገቡ እምርታዎች ዜጎች በሀገራቸው ላይ በትልቁ ተስፋ እንዲያደርጉ ማስቻሉ ይታያል። ይበል የሚያሰኘው እምርታዊ ግስጋሴ በተያዘው አዲሱ የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ በመቀጠል የኢትዮጵያን ትንሳኤ እንደሚያፋጥን የነዋሪዎቹ እምነት ነው።
በማሬ ቃጦ