በሩስያ የሚገኝ የመድሀኒት አምራች ኩባንያ በክሊኒካል ሙከራ ደረጃ 100 በመቶ ውጤታማ የሆነ የአንጎል እጢ ካንሰር ክትባት ማግኘቱን አስታወቀ።
“ኢንትሮሚክስ” በመባል የሚታወቀው የክትባት አይነት የካንሰር ሴልን የሚያጠፋ ቫይረስ በመፍጠር እድገቱን ባለበት ለማቆም እና ቀስበቀስ ከሰውነት ውስጥ እንዲጠፋ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
ሩስያ ቱደይ ይዞት በወጣው ዘገባ ክትባቱ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ የሀገሪቱን የጤና ሚኒስቴር ማረጋገጫ ካገኘ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ወደ ምርት እንደሚገባ ተመላክቷል።
ከኮቪድ 19 ክትባት ከተገኘ ልምድ የተቀመረ ነው የተባለው ይህ ክትባት በሚሊየን ለሚቆጠሩ ካንሰር ህመምተኞች ተስፋን የሚሰጥ ሆኗል።
ክትባቱ ባለፉት አመታት በምርምር እና ሙከራ ደረጃ የተለያዩ ሂደቶችን ያለፈ ሲሆን፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው መረጋገጡ ተመራጭ ሊያደርገው እንደሚችል ነው የተነገረው።
ከአንጎል እጢ ካንሰር በተጨማሪ ለሳምባ፣ ለጡት፣ ለፓንክሪያቲክ እና ሌሎችም የካንሰር አይነቶች ክትባቱ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል።
በ2023 የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአለም ላይ 9.7 ሚሊየን ሰዎች በካንሰር ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
በዳዊት በሪሁን